ለኦርቶዶክሳውያን እና ለቤተክርስቲያን ክብር በመሟገታቸው ለእስር ተዳርገው የነበሩት ፓስተር ብንያም ሽታዬ ከእስር ተለቀቁ።
ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በተደጋጋሚ ጥብቅና በመቆም ሉዓለዊነቷንና መብቷን ማስጠበቅ እንደሚገባ በመሟገታቸው ሁካታና ብጥብጥ ፈጥረዋል በሚል ወቀሳ ታስረው የነበሩት ፓስተር ብንያም ሽታዬ ዛሬ የካቲት ፲፯፤ ፳፻፲፭ በአምስት ሽህ ብር ዋስ ተለቀዋል፡፡ ለዚህም ውሳኔ መሳካት ከፍተኛ ርብርብ ያደረጉት ፴፫ የሚሆኑ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ የሕግ ጥበቆች መሆናቸው ታውቋል፡፡
ፓስተር ብንያም ከዚህ ቀደምም የመስቀል ዐደባባይ የመሬት ይዞታ ጥያቄም ይሁን በዚህ ወቅት ቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት የመብትና የማንነት ጥየቄ መሆኑን አስረድተው “ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ሀገር ናት፤ እንደ ሌሎች መጤ አይደለችም፤ ታሪክ የሚያውቅ ካለም ማንም ይሞግተኝ” በማለት በዐደባባይ ተከራክረዋል።
ወንጌል በሰላምና በፍቅር መኖርን እንጂ የሌላውን መብት በመጋፋት ሁካታና ሽብር ወይም ብጥብጥ መፍጠርን እንደማያስተምር የሚያስረዱት ፓስተር ብንያም በተለያዩ መገናኛ ብዙኃናት ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የሚመለከቱ ክሶችን በመቃወም ይታወቃሉ።