የካቲት ፳፫ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም
****
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
“””””””””””””””””””””
የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖትን ፲ኛ ዓመት በዓለ ሢመት በማስመልከት በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት በተቋቋመው የሥነ ጽሑፍ ዝግጅት ኮሚቴ ተዘጋጅቶና በሊቃውንት ጉባኤ ተመርምሮ የተዘጋጀውና ለህትመት የበቃው ዜና መዋዕል ዘብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ መጽሐፍና የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቃለ በረከት መጽሐፍ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ሚኒስትሮች ፣አምባሳደሮች፣የጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያና የድርጅት ኃላፊዎች፣የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ኃላፊዎች፣የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ፣የወጣት ማኅበራት ተወካዮችና የክብር እንግዶች በተገኙበት ዛሬ የካቲት ፳፫ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም በታላቅ ድምቀት ተመርቋል።

በምርቃት መርሐ ግብሩ ላይ ከመጻሕፍቱ ውስጥ ከልደት እስከ ፓትርያርክነት ያለው የቅዱስነታቸው ታሪክ፣በተለያዩ ወቅቶች ያስተላለፏቸው ታሪካዊ ቃለ በረከቶች በንባብ የተሰሙ ሲሆን በመጻሕፍቱ ዝግጅትና ሕትመት ወቅት ጉልህ ድርሻ ላበረከቱ አካላት የእውቅናና የምስጋና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።

የተዘጋጁት መጽሐፍት የቅዱስነታቸውን የህይወት ታሪክ፣ባለፉት ፲ዓመታት በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገራት ያከናወኗቸውን ዋና ዋና ሥራዎችን፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎችን፣ቤተክርስቲያናችን ባለፉት ፲ዓመታት በስኬት ያከናወነቻቸው ዋና ዋና ተግባራትና የገጠሟትን ተግዳሮቶች ተከትሎ በቅዱስ ፓትርያርኩ የተላለፉ መልዕክታትን አጠቃሎ የያዘ ሲሆን ለታሪክ፣ለምርምርና ለቋሚ ሰነድነት እንዲያገለግል ተደርጎ በጥሩ የገጽ ቅንብር ተከሽኖ ዓለም አቀፍ ደረጃን በሚያሟላ መልኩ የታተመ ቋሚ ሰነድ ነው።እነዚሁ መጻሕፍትን በውጪው ዓለም የሚገኙ ምዕመናን በቀላሉ አጊንተው ማንበብ ይችሉ ዘንድም በቤተክርስቲያናችን ድረ ገጽ https://eotceth.org ላይ እንዲጫን ተደርጓል።

“የቅዱስነታቸው በረከትና ረድኤት ከሁላችን ጋር ይሁን።”