በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የማኅበራት ምዝገባና ክትትል መምሪያ ቀጣዩን የሥራ አተገባበር አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያ የማኅበራት ምዝገባና ክትትል መምሪያ በጥቅምት ወር ፳፻፲፭ ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ ዕውቅና ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ የውስጥ አሠራሩን ሲያመቻች የቆየ መሆኑን የሕግ ባለሙያው አቶ አያሌው ቢታኒ ሐምሌ ፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

የሕግ ባለሙያው አቶ አያሌው ቢታኒ ከዚሁ ጋር አያይዘው እንዳብራሩት የማኅበራት ምዝገባና ክትትል መምሪያ የመተዳደሪያ ደንብና የአፈጻጸም መመሪያ ተዘጋጅቶለታል።
ለተመዝጋቢ ማኅበራትም ሞዴል የሚሆን ቅጽ ተዘጋጅቷል ያሉት የሕግ ባለሙያው ወደ ምዝገባ የሚገቡ ማኅበራት የጠቅላላ አባላቱ ቁጥር ሰባት መቶ ሀምሣ እና ከዚያ በላይ የሆኑ ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታይ መሆናቸው በማስረጃ የተረጋገጠላቸው፣የንስሐ አባት የያዙ፣ በትምህርተ ሃይማኖት በቂ ዕውቀት ያላቸው ይሆናሉ ብለዋል።

አቶ አያሌው ቢታኒ በሰጡት ማብራሪያ አክለው እንደገለጹትም በማኅበራት ምዝገባና ክትትል መምሪያ ከሚካተቱት የማኅበራት ዘርፎች ከስምንት ያላነሱ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የማኅበራት አንድነት፣የሙያ ማኅበራት፣የበጎ አድራጎት ማኅበራት፣የሐዋርያት ማኅበራት ፣መንፈሳዊ አስጎብኚ ማኅበራት ይገኙባቸዋል።

ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የደቡብ ትግራይ ማይጨው እና ደቡብ ምሥራቅ ትግራይ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የማኅበራት ምዝገባና ክትትል መምሪያ የበላይ ሐላፊ ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት የማኅበራት ምዝገባና ክትትል መምሪያ ዋና ዓላማው ልዩ ልዩ ፈተና በበዛበት በዚህ ዘመን ምእመናን አንድነታቸውን እያጠናከሩ ባንድ ላይ በመቆም ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ እንዲረዳቸው ታስቦ ሲሆን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንንም ባንድ ላይ ሆነን ለማሻገር እንድንችል ነው ብለዋል።