ቅዱስ ሲኖዶስ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ሲያደርግ የነበረውን አስቸኳይ ጉባኤ በማጠናቀቅ መግለጫ ሰጠ።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

በክልል ትግራይ በተካሄደው ጦርነት በቤተ ክርስቲያናችን የበላይ መዋቅርና በክልል ትግራይ አህጉረ ስብከት መካከል የነበረው አስተዳደራዊ መዋቅር ተቋርጦ መቆየቱን ተከትሎ የተፈጠረው አለመግባባት በውይይት ተፈቶ መዋቅራዊ አንድነታችን በድጋሚ ተጠናክሮ እንዲቀጠል ሀገራዊ የሰላም እርቁ ከተፈጸመበት ማግስት ጀምሮ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ፊርማ በተደጋጋሚ በደብዳቤ ሲጠየቅ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

ምንም እንኳን ቅዱስ ሲኖዶሱ ችግሩ በውይይት እንዲፈታ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ሲያደርግ የቆየ ቢሆንም በክልሉ ያሉት ብፁዓን አባቶችና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በተከፈተው የሰላምና የውይይት በር ከመጠቀም ይልቅ መዋቅራዊ አደረጃጀቱን በመጣስ መንበረ ሰላም የትግራይ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት መሥርተናል በሚል ተገቢነት የሌለው መግለጫ ከመስጠትም አልፎ ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳት መፈጸም አለበት የሚል ውሳኔ በማሳለፍ 10 ኤጲስ ቆጶሳትን ሐምሌ 9 ቀን 2015 ዐ.ም. ለመሾም ፕሮግራም መያዙን በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን መግለጫ መስጠታቸውን ተከትሎ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሰኔ 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ በጦርነቱ ወቅት ለነበረው የመዋቅራዊ ግንኙነት ጉድለትና የሰብአዊ ድጋፍ እጥረት በይፋዊ መግለጫ ይቅርታ የተጠየቀ ቢሆንም ለይቅርታው አዎንታዊ ምላሽ አለመሰጠቱ በእጅጉ አሳዛኝ መሆኑ፤

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለችግሩ መፈታት ባላት ቁርጠኝነት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የሚመራ የሰላም ልዑክ ወደ ክልሉ በመላክ በክልሉ ለደረሰው ጉዳት ሰብአዊ ድጋፍ የሚውል ብር20,000,000.00(ሃያ ሚሊየን ብር) ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ያስረከበች ሲሆን በዚህም ወቅት ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ለተደረገው የከበረ አቀባበል ቅዱስ ሲኖዶስ አመስግኗል፡፡

ይሁን እንጁ የሰላም ልዑኩ ዋና ተልእኮ የሆነውን በክልሉ ከሚገኙ ብፁዓን አባቶች ጋር ለመወያየት የተያዘውን አጀንዳ በተመለከተ በብፁዕ ወቅዱስ አባታችን የተመራው የሰላም ልዑክ በመቀሌ ሀገረ ስብከት በደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል የተገኘ ቢሆንም ቤተ ክርስቲያን በመዘጋቱ ምክንያት ቅዱስ ሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባኤ በእጅጉ አዝኗል፡፡

በመሆኑም የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ አንቀጽ 19 ንዑስ ቁጥር 13 የሕግ ድንጋጌ መሠረት ሐምሌ 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፏል፡፡

1. በትግራይ ክልል ሐምሌ 9 ይደረጋል የተባለው የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ የሕገ ቤተ ክርስቲያንና አንቀጽ 37 እና 38 ያላከበረና ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን አንጻር ተገቢ ያልሆነ የቤተ ክርስቲያንን ማዕከላዊነት የሚጥስ፣ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚጎዳና በጦርነት የተጎዳውን ሀብት ንብረቱ የወደመበትን ገዳማቱና አብያተ ክርስቲያናቱ የተጎዱበትን ሕዝብ የማይጠቅም ተገቢነት የሌለው በመሆኑ እንዲቆም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

2. በትግራይ ክልል ተከስቶ የነበረውን ችግር የፌዴራል መንግሥትና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ችግሩን በውይይት የፈቱት መሆኑ እየታወቀ የሰላም ባለቤት የሆነችው ቤተ ክርስቲያን እስካሁን ሰላም መፈለጓ ያልተቋረጠ ቢሆንም አለመሳካቱ የሚያሳዝን በመሆኑ ለሰላም የሚደረገው ጥረት ዘላቂ መፍትሔ እስከሚገኝ ድረስ የማይቋረጥ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ይገልጻል፡፡

3. በመሆኑም ክቡር የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ እና ክቡር አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እንዲሁም የፌዴራልና የክልሉ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እየተደረገ ያለውን ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ያልተከተለ የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ እንዲያስቆሙልን ብሎም ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ችግሮቹ በውይይት እንዲፈቱ መንግሥታዊ እገዛ በማድረግ የውይይት መድረክ እንዲያመቻቹልን ሲል የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

4. በመላው ዓለም የምትገኙ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ሕዝበ ክርስቲያን እናት ቤተ ክርስቲያናችሁ ያስተላለፈችውን የሰላም ጥሪ ተግባራዊ ሆኖ አንድነቷ ጸንቶ ይኖር ዘንድ በጸሎት ተግጋችሁ ከቤተ ክርስቲያናችሁ ጎን እንድትቆሙ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ሐምሌ 6 ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ