ጳጉሜን ፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ/ም

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት በ፳፻፲፭ ዓ/ም የሥራ ዓመት በነበረው የሥራና የአገልግሎት አፈጻጸም ዙሪያ አጠቃላይ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሠራተኞች በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አሥኪያጁ በብፁዕ አቡነ አብርሃም መሪነት በጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ ሠፊ ውይይት አደረጉ።
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ባደረጉት የመግቢያ ንግግር “ስለ እግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት በጀመረው ሥራ ሁሉ፥ በሕጉና በትእዛዙም፥ አምላኩን ለመፈለግ በፍጹም ልቡ አደረገው፥ ተከናወነለትም።” 2 ዜና 31÷21

“እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ፥ የሚሄድበትም መንገድ ተከናወነለት፤” 2 ነገሥት 18÷7 የሚሉትን የቅዱሳት መጻሕፍት መልእክቶች መነሻ በማድረግ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሠራተኞች የተሠማሩት ሥራ ላይ ብቻ ሳይሆን አገልግሎትም በመሆኑ ተከናውኖልናል ወይ ብለው መጠየቅ እንዳለባቸውና ክንውን የሚገኘውም ሥራን በታቀደው መሠረት በአግባቡ በማከናወንና እግዚአብሔርን አጥብቆ በጸሎት ደጅ በመጥናት መሆኑን አበክረው ገልጸዋል።
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አክለውም እያጠናቀቅን ባለው ዓመት በተያዘው ዕቅድ መሠረት የተፈጸመው ሥራዎች ያሉትን ያህል ያልተፈጸሙ ብዙ ሥራዎች በመኖራቸው የሥራ አፈጻጸም ላይ ጠንካራ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው በመግለጽ መመሪያ ተሰጥተዋል።
በስብሰባው ላይ “ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ” ኤፌ. 5÷16 የሚለውን የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት መነሻ በማድረግ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቧል። ጽሑፍ አቅራቢው መ/ሰ አባ ቃለጽድቅ ሙሉጌታ (ዶ/ር) የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ኃላፊ ይህን ከዕለት ዕለት እየከፋ የመጣውን ዘመን ለመዋጀት አስፈላጊው ነገር ጥበብ፣ ጥንቃቄ፣ ጸሎት፣ በምስጋና፣ ለሌሎች ብርሃን በመሆን፣ ባለመጨነቅና በመታመን መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍትን ዋቢ በማድረግ አስረድተዋል።
በመቀጠልም ለቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ የመነሻ ሀሳብ ያመነጩት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒው ዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ዘመንን እንዴ መዋጀት እንደሚገባ አባታዊ መንፈሳዊ መልእክት አስተላልፈዋል። ብፁዕነታቸው በመልእክታቸው የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሠራተኞች ለቀጣዩ ዓመት ሥራቸውን በተቀመጠው ዕቅድ መሠረት ለመሥራት ለእግዚአብሔር ቃል መግባት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የሕግ አገልግሎት መምሪያ ኃላፊው አፈ መምህር አባ ገብረሥላሴ በዓመቱ ቤተክርስቲያን የምትመራባቸውን ሕግጋት ለማሻሻልና በዓመቱ የገጠማትን ፈታኝ ወቅት እንድታልፍ የሠራቸውን ሥራዎች የሚያስገነዝብ ገለጻ አድርገዋል። አክለውም በዓመቱ ከቀረቡ የክስ አቤቱታዎች መካከል የሁለቱ ግለሰቦች ምርመራ ተጠናቆ ለአቃቤ ሕግ የቀረበ ሲሆን የአንዱ ደግሞ በሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
በስብሰባው በሊቀ አእላፍ በላይ መኮንን የጠቅላይ ቤተክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ መሪነት የጉባኤው ተሳታፊዎች በሰጡት የተቆርቋሪነት ሀሳብ የጠቅላይ ጽ/ቤቱን መንፈሳዊ ዕቅድ ዳር ለማድረግ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ የሚቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
በጉባኤው የእህታማቾች ዘማርያን ሕብረት መዘምራን የእንቁጣጣሽ ዝማሬ በማቅረብ ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬ ተቀብለዋል።