መስከረም ፬ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ዓ.ም
“””””””””””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
******
በየዓመቱ መስከረም ፲፮ ቀን በታላቅ ሃይማኖታዊ ሥነሥርዓት የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል በአገር አቀፍ ደረጃ በመስቀል አደባባይ ቅዱስ ፓትርያርኩ ፣ብፁዐን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣የመንግስት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣የከተማችን አስተዳደር ከንቲባ፣
አምባሳደሮች፣ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች፣
ካህናት፣የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ምዕመናንና ምዕመናት በተገኙበት እንደሚከበር ይታወቃል።

በዓሉ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ በድምቀት ተከብሮ ይውል ዘንድም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ዐቢይና ንዑሳን ኮሚቴዎችን በማደራጀት በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ስታከናውን ቆይታለች።

የዐቢይ ኮሚቴ አባላቱም በስራቸው የተደራጁ ንዑሳን ኮሚቴዎችን በማስተባበርና ተለይቶ የተሰጣቸውን ሥራዎች በማከናወን ለዐቢይ ኮሚቴው በሪፖርት ሲያሳውቁና የተግባራቶቻቸውን አፈጻጸም መሰረት ያደረገ ሥራ ሲያከናውኑ ቆይተዋል።በተለይም በቀጥታ ከበዓል አከባበሩ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን የሚያከናውኑ ማለትም የካህናት ፣የሰንበት ትምህርት ቤት፣የሥነ ጽሑፍ፣የደመራ ዝግጅት፣ የእስቴጅ ዝግጅትና የባጅ ዝግጅት ንዑሳን ኮሚቴዎች አስፈላጊውን ሥራ ሁሉ ቀድመው ማከናወናቸውን መነሻ ያደረገ የእቅድ ክንውን ግምገማ በዛሬው ዕለት በጠቅላይ ቤተክህነት ጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ ተከናውኗል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም የዐቢይ ኮሚቴው ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ አብርሃምና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒዩወርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ዶ/ር ተገኝተዋል።

በእቅድ አፈጻጸም ግምገማው ላይ በዓሉን በድምቀትና ሰላማዊ በሆነ መልኩ ለማክበር ይቻል ዘንድ አስቀድሞ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።በቀሪ ቀናት የሚከናወኑ ሥራዎችም በፍጥነትና ሕግና መመሪያን በጠበቀ አግባብ እንዲከናወኑም በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አቅጣጫ ተቀምጧል።

በእቅድ አፈጻጸም ግምገማው ላይ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ እንደገለጹት በዓሉ ሃይማኖታዊና አገር አቀፋዊ መሆኑን መሰረት ያደረገ ሥራ መከናወን እንደሚገባው ጠቁመው በዓላችን ዓለም አቀፋዊ እውቅና ያለውና ለአገራችን ገጽታ ግንባታም ጉልህ ድርሻ የሚያበረክት መሆኑን አስታውሰው የበዓል አከባበሩ ሂደት ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን የጠበቀና ፍጹም ሰላማዊ መሆን ይችል ዘንድ ከዐቢይ ኮሚቴው ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ የቤተክርስቲያናችን የሥራ ኃላፊዎች በትጋት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል ።

ወጣት የቤተክርስቲያን ልጆችም ከማዕከላዊ የቤተክርስቲያናችን አስተዳደር የሚሰጡ መመሪያዎችን በማክበርና መርሐ ግብሩ በተያዘለት ዕቅቅ መሰረት መከናወን ይችል ዘንድ የሚጠበቅባቸውን ሃይማኖታዊ አክተዋጽኦ በፍጹም ክርስቲያናዊ ጨዋነት ማበርከት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በዓላችን በደመቀ መልኩ ያለ አንዳች የጸጥታ ችግር ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድም ሁላችንም ሕግ አስከባሪ፣ሁላችንም ጸጥታ አስከባሪና አስተባባሪ በመሆን ከመስራት ጀምሮ የመንግስት የጸጥታ አካላት ሰላምና ጸጥታን ለማስከበር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በቀና መንፈስ በመደገፍ በዓላችን ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም እንዲከበር ማድረግ ይኖርብናል ካሉ በኋላ በመንግስት የጸጥታ አካላት የማይፈቀዱ ማናቸውንም ተግባራት ባለመፈጸምም ሕግ አክባሪነታችንን በተግባር ማሳየት ይኖርብናል ብለዋል።

በመርሐ ግብር አተገባበር ዙሪያ በየጊዜው የሚስተዋሉ መጓተቶች አግብብ አለመሆናቸውን የጠቆሙት ብፁዕነታቸው ያስቀመጥነውን የጊዜ መርሐ ግብር ማክበርና ማስከበር ከሁላችንም የሚጠበቅ መሆኑን በመገንዘብ ለተግባራዊነቱ የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ጨምረው ገልጸዋል።

የዘንድሮ የመስቀል ደመራ በዓላችን ሙስሊም ወገኖቻችን የመውሊድ በዓልን ከሚያከብሩበት ቀን ጋር የተገጣጠመ በመሆኑ በዓላችንን ፍጹም ሰላማዊ በሆነና የቀደመ መከባበርና መቻቻላችንን መሰረት ባደረገ አግብብ በፍቅር ማክበር ይኖርብናል ያሉት ብፁዕነታቸው የበዓል አከባበር ሒደቱን በማስመልከትም በቤተክርስቲያናችን የመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ከወዲሁ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብሮች እንዲከናወኑ ይደረጋል ብለዋል።በማያያዝም ሁሉም የበዓሉ ታዳሚና በበዓሉ ላይ ትርኢት የሚያቀርቡ አካላት ሁሉ የቤተክርስቲያናችንን አርማ ብቻ ሊጠቀሙ ይገባል ብለዋል።

ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ዶ/ር በበኩላቸው በዓላችን ፍጹም ሃይማኖታዊ በመሆኑ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ አግባብ ብቻ እንዲከበር ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸው ስለበዓላችን አጠቃላይ እንቅስቃሴና የአከባበር ሂደት የቤተክርስቲያናችን ሚዲያዎች አስቀድመው ዝርዝር ማብራሪያዎችና የግንዛቤ ማሳደጊያ መልዕክቶችን ማስተላለፍ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።