መስከረም ፰ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
“””””””””””””””””””””””””””””””
አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ
******
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል የቅድመ ዝግጅት ሥራውን እያከናወነ ነው።

መምሪያው በዛሬው ዕለት በታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም የምሥራቅ ክፍለ ከተማ የመዝሙር ጥናቱን ያካሔደ ሲሆን በጥናት መርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስና የመምሪያው ዋና ኃላፊ መ/ብ ቆሞስ አባ ተክለያሬድ ዘጎርጎሬዎስ ተገኝተዋል።

የጥናት መርሐ ግብሩም ከታዕካ ነገሥት ቷዓታ ለማርያም ቤተክርስቲያን በተጨማሪ በከሰዓት በኋላ መርሐ ግብር በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የሰሜን ክፍለ ከተማ የወጣቶች የመዝሙር ጥናት መርሐ ግብር በመካሔድ ላይ ይገኛል።

በአጠቃላይ አሁኑ ጊዜ በ5 የጥናት ማዕከላት በዚህ መልኩ የጥናት መርሐ ግብሩ እየተካሔደ የሚገኝ ሲሆን የመዝሙርና የመንፈሳዊ ትርዒቱ በሚጀመርበት ጊዜ ሁሉ በየቀኑ የጸሎትና የትምህርት መርሐ ግብር ይከናወናል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ሰብሳቢነት በሚመራው ዐቢይ ኮሚቴ አማካኝነት የበዓሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራ በሚገባ እየተመራና አፈጻጸሙ በየጊዜው እነተገመገመ ሲሆን በቀናት በፊትም የሁሉም ንዑሳን ኮሚቴዎች የዕቅድ አፈጻጸም ተገምግሞ በቀሪ ቀናት የሚከናወኑ ሥራዎች አቅጣጫ የተሰጠባቸው መሆኑ ይታወሳል።

በዚህም መሰረት በዓሉ ፍጹም ሃይማኖታዊና ታሪካዊ በዓል መሆኑን ታሳቢ ባደረገ አግባብ ሕግና ሥርዓት ተከብሮ እንዲሰራ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ መመሪያ መሰጠቱ ይተወሳል።በተለይም ደግሞ የዘንድሮ የመስቀል ደመራ በዓል ሙስሊም ወገኖቻችን የመውሊድን በዓልን ከሚያከብሩበት ወቅት ጋር የተገጣጠመ በመሆኑ በመተሳሰብና በመተጋገዝ ፍጹም ክርስቲያናዊ ሥነምግባርን በተላበሰ አግባብ በዓላችንን እንድናከብር ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አደራ ማለታቸው ይታወሳል።