ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል የጋምቤላ፣የአስሳ፣የቄለም ወለጋና የደቡብ ሱዳን አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በደምቢዶሎ ከተማ በሚያደርጉት ሐዋርያዊ አገልግሎት በደምቢዶሎ ከተማ ቀበሌ03 በአርባ ቀናት ተሰርቶ የተጠናቀቀውን የቅዱስ አማኑኤል ቤተክርስቲያን መስከረም 6ቀን 2016ዓ.ም ቅዳሴ ቤቱን ማክበራቸውን የሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት ሕዝብ ግንኙነት ክፍል በላከልን ዘገባ ገልጿል።አያይዞም በሀገረ ስብከቱ ከማገኙ 13ወረዴዎች መካከል የቅዱስ ሲኖዶስን መዋቅር በመተው በኦሮሚያ ሲኖዶስ ስር እንገለገላለን በማለት ከቅድስት ቤተክርስቲያን ተነጥለው የሰነበቱ ሊቃነ ካህናት በድርጊታቸው በመጸጸት አንድ ፓትርያርክ ፣አንድ ሲኖዶስ፣አንድ መንበር፣አንዲት ቤተክርስቲያን በማለት ወደ እናት ቤተክርስቲያን ተመልሰዋል ብሏል።

ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል መስከረም 10 ቀን 2016ዓ.ም የከተማዋ ከንቲባና የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊው በተገኙበት አዲሱ የትምህርት ዘመንን መጀመር በማስመልከት ወላጅ አልባና ረዳት ለሌላቸው እጓለማውታ ልጆች ሃያ ካርቶን ደብተርና እስኪርቢቶ በመግዛት ድጋፍ ማድረጋቸውን የገለጸው ዘገባው የከተማ አስተዳደሩ ለሀገረ ስብከቱ ባበረከተው ሃያ ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያንን ለመትከልና መዋዕለ ሕጻናት ትምህርት ቤት ለመክፈት ብፁዕነታቸውና የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጣቸውን ዘገባው አመልክቷል።

በተያያዘ ዜና በደንቢዶሎና በቄለም ወለጋ የሚገኙ አድባራትና ገዳማት የሚገኙ ካህናት፣ የምዕመናን ተወካዮች፣የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ባደረጉት ስብሰባ የቤተክርስቲያንን አንድነትና ህልውና በማጽናት ለሰላምና ለአንድነት በጋራ እንደሚቆሙ ገልጸው ፓትርያርካችን አቡነ ማትያስ ጳጳሳችንም አቡነ ሩፋኤል ናቸው።ከአሁን በፊት ከሲኖዶስ እውቅና ውጪ የተሾሙትን አንቀበልም።የሚል የአቋም መግለጫ በማውጣት ውይይታቸውን ማጠናቀቃቸውን የሀገረ ስብከቱ ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ገልጿል።

ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል በከተማው ቀበሌ 04 አካባቢ ለሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት መገልገያ የሚሆን ሕንጻ በአራት ሚሊየን ብር መግዛቱን የገለጸው የሀገረ ስብከቱ ዘገባ ሕንጻውን በቅዱስ ፓትርያርኩ በቅርቡ ለማስመረቅ ሀገረ ርብከቱ በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጿል።

ብፁዕነታቸው ባለፉት ሁለት ወራት በሀገረ ስብከቱ ሲያካሒዱ የቆዩትን ሐዋርያዊ አገልግሎት ከመስከረም 15 ቀን ጀምሮ በማጠናቀቅም በጋምቤላና አሶሳ አህጉረ ስብከት ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በመቀጠል በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ ጠቅላይ ቤተክህነት የሚያቀኑ ይሆናል ሲል የሀገረ ስብከቱ ሕዝብ ግንኙነት ክፍል በላከልን ዘገባ ጨምሮ ገልጿል።