ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሰሜን አሜሪካ ሲያደርጉት የቆዩትን ሕክምና አጠናቀው ዛሬ ማለዳ ወደ አገራቸውና ወደ ወንበረ ክብራቸው በሰላም ተመለሱ።

ቅዱስ ፓትርያርኩ ዛሬ ማለዳ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ዶ/ር የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒዩወርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣የጠቅላይ ቤተክህነት መምሪያ ኃላፊዎች፣ክቡር መልአከ ሕይወት አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ የቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ደማቅ አቀባበል ከድርገውላቸዋል።

በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳምም ለቤተክርስቲያንና ለቅዱስነታቸው ክብር የሚመጥን የእንኳን ደህና መጡ መርሐ ግብር ከሰዓታት በኋላ የሚከናወን ይሆናል።

ቅዱስ ፓትርያርኩ ወደ አሜሪካ ያቀኑት ከአንድ ዓመት በፊት ተይዞላቸው በነበረ የህክምና ቀጠሮ ምክንያት ነው።
አንዳንድ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ከቅዱስነታቸው ጉዞ ጋር በተያያዘ ቅዱስነታቸው ተመርዘው ወደ አሜሪካን ለህክምና እንደ ተጓዙ አስመስለው መሰረተ ቢስና ከእውነት የራቀ መረጃዎችን በማስተላለፍ ሕዝበ ክርስቲያኑን ሲያደናግሩ መክረማቸውም ይታወሳል።