ጥቅምት ፬ ቀን ፳፻ ፲ ወ ፮ ዓ.ም
“””””””””””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
******
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዶግማ፣ ቀኖና፣ ሕግና ደንብ የሚመራ “ፍኖተ ጽድቅ ብሮድካስት አገልግሎት ” የተሰኘ የቴሌቪዥን ድርጅት ሊያቋቁም ነው።

ድርጅቱ የሚያቋቁመው ዘመናዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ የሚተዳደርበት ደንብና የሚዲያ ሥራውን የሚያከናውንበት ኤዲቶሪያል ፓሊሲ የቤተ ክርስቲያናችንን ዶግማ፣ቀኖና፣ሕግና መመሪያን መሠረት ያደረገ ሆኖ መዘጋጀት ይችል ዘንድ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መምሪያ ኃላፊዎች፣ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ፣ከታዋቂ ሰባኪያን፣ከታላላቅ የአገራችን የቴሌቪዥን ድርጅት የሥራ ኃላፊዎች የተውጣጣ ኮሚቴ እንዲቋቋም ተደርጓል።

በዚሁ ኮሚቴ ተዘጋጅቶ የቀረበው ረቂቅ መተዳደሪያ ደንብና ኤዲቶሪያል ፓሊሲ ለቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦ ከጸደቀ በኋላ በስራ ላይ የሚውል ሲሆን ፍኖተ ጽድ ብሮድካስት አገልግሎትም ደንብና መመሪያዎችን አክብሮ የመስራት ግዴታ ይኖርበታል።

ተዘጋጅተው የቀረቡት የማቋቋሚያ ደንብ እና ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ፍኖተ ጽድቅ የብሮድካስት አገልግሎት የበቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖናና ትውፊት ብቻ ማእከል አደርጎና በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ታቅፎ እንዲያገለግል የሚደረግ ከመሆኑም በላይ፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የፍኖተ ጽድቅ የብሮድካስት አገልግሎትን መከታተል፣ መቆጣጠር ፣ ማገድና መሰረዝ የሚያስችሏትን መብት የሚሰጣት ነው ።

በባለሙያዎቹ ተጠንቶ የተዘጋጀው ኤዲቶሪያል ፖሊሲ በፍኖተ ጽድቅ በሚዘመሩ መዝሙራት እና የመዝሙር መሣሪያዎች ላይ የሚታዩ አንዳንድ ክፍተቶችን የሚያርም ብቻ ሳይሆን ከዚህ በኋላም ለአገልግሎት የሚውሉ መዝሙራትና የመዝሙር መሣሪያዎች በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የተፈቀዱ ብቻ መሆን እንደሚገባቸው መደንገጉን ከፖሊስው መረዳት ተችሏል።

በትላንትናው ዕለት በሀርሞኒ ሆቴል በተፈጸመው የማቋቋሚያ ደንብ እና ኤዲቶሪያል ፖሊሲ የሰነድ ርክብክብ ላይ ብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስ የምሥራቅ ሽዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የደቡብና የደቡብ ምሥራቅ ትግራይ፣ የቤተመጻሕፍት ወመዘክርና የማኅበራት ማደራጃ ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ኢሉ አባቡራ፣ቡኖ በደሌና በሰሜን አሜሪካ የሜኒሶታና አካባቢው አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ የኢትዮጵያ ሱማሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ሊቀ አእላፍ በላይ መኮንን የጠቅላይ ባቤተክህነት ም/ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ሊቀትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፣ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጠቅላይ ጸሐፊ፣የጠቅላይ ቤተ ክህነት መምሪያ ኃላፊዎች፣የማኅበራት ተወካዮች ተገኝተዋል።

በዚሁ ጊዜም በረቂቅ ማቋቋሚያ ደንቡና በኤዲቶሪያል ሰነድ ዝግጅት ላይ ለተሳተፉ ባለሙያዎችና የበኩላቸውን ድጋፍና ትብብር ላደረጉ አካላት የምስጋና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ረቂቅ ሰነዱ በ”ፍኖተ ጽድቅ” በበይነ መረብ ሚዲያ ይተላለፉ የነበሩ ክፍተቶችን አርሞ ከማስቀጠልና በቤተ ክርስቲያናችንም ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ሰነድ እንደሆነም ተገልጿል። በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ከዚህ በኋላ የፍኖተ ጽድቅ ጉዳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ነው ብለዋል።