፵፪ ኛው ዓለምአቀፍ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ

ለ፵፪ ኛ ጊዜ የሚካሔደው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዓለም አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የተዋጣለት፣የተሳካና ውጤታማ በሆነ መልኩ መከናወን ይችል ዘንድ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎቹ በሚገባ ታቅደው፣ ለእያንዳንዱ ተግባር አስፈጻሚና ፈጻሚ አካል ተቀምጦለት የተከወነ ከመሆኑም በላይ የእያንዳንዱ ኮሚቴ የሥራ አፈጻጸምና አጠቃላይ የቅድመ ዝግጅት ሥራው አፈጻጸም በብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሚመሩት አስተዳደር ጉባኤ ተገምግሞ ማስተካከያ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ከተስተካከሉና ከታረሙ በኋላ ወደ ተግባር እንዲለወጡ ተደርጓል፤ ይህም በመደረጉ እያንዳንዱ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ያማረና የተዋበ እንዲሆን ማድረግከመቻሉም በላይ በአፈጻጸም ደረጃም ውጤት የተመዘገበበት መሆን ችሏል።

ጉባኤው ውጤታማ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር እንዲረዳን በየዕለቱ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ጸሎትና ቡራኬ ተከፍቶ በቅዱስነታቸው ሊቀ መንበርነትና መመሪያ መሠረት እየተካሄድ ይገኛል ፡፡

በተለይም ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ጉባኤውን ፍትሐዊ በሆነ መልኩ በመምራታቸው የሰዓት መዛነፍና የተንዛዛ ሪፖርት እንዳይቀርብ ማድረግ ያስቻለ ሲሆን ከመርሐ ግብር ውጪ የሆኑና መስመራቸውን የሳቱ እንዲሁም ከእውነተኝነት የራቁ ሪፖርቶችን በማረቅ ሐቁ በግልጽ እንዲቀመጥ ያደረጉበት ጥረትም የብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁን የጉባኤ አመራር ጥበብና ብቃት ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ተግባር ሆኖ ተመዝግበዋል። ጉባኤውም በተደጋጋሚ ጊዜ ይህን ሐቅ በጭብጨባ ሲገልጽ ተስተውሏል።

ሌላውና በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ዘመነ ሢመት ሥር ነቀል ማስተካከያ የተደረገበት ከዚህ በፊት ተጀምሮ መቀጠል የተሳነው ብዙዎች በየዓመቱ በሚካሔደው ጉባኤ ሲተቹት የሚሰማው ውይይት ለምን አይደረግም? የገንዘብ ሪፖርት ብቻ ነው የሚሰማው፣ ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎችን የመለሰና በቡድን የተደረገ ውይይትን በጋራ ማብራሪያ የሚሰጥበት አሠራር ተጠናክሮ እንደገና የተጀመረው በብፁዕ አቡነ አብርሃም የአመራር ዘመን እንደሆነ እርግጥ ነው።

በዘንድሮ ዓለም አቀፍ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይም ልዩ ልዩ ወቅታዊ ጥያቄዎችን በማንሣት ውይይት ቢቀር ጥሩ ነው የሚል ዐሳብ ያነሡ የነበሩ ብዙዎች ቢሆኑም ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ግን ውይይት ሊፈራ አይገባውም። መለመድ አለበት። ችግሮች መፍትሔ የሚያገኙት በውይይት ነው።ስለዚህ ውይይት መካሔድ አለበት የሚል ጽኑዕ አቋም በማራመዳቸው የጋራም የቡድንም ውይይት በ፵፪ ኛው ዓለም አቀፍ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ እንዲካሔድ በአስተዳደር ጉባኤ ተወስኖ በመርሐ ግብሩ ተካቶ እነሆ ተፈጻሚ የሚሆንበት ጊዜ ሰሌዳ ላይ ደርሰናል።

በሚደረገው የቡድንም ሆነ የጋራ ውይይት ችግሮቻችንን የምንመለከትበት፣ለችግሮቻችን መፍትሔ የምንሰጥበት ሁኔታ እንደሚፈጠርም በዛሬው ዕለት በተጀመረው የውይይት መርሐ ግብር ላይ የተነሡት ዐሳቦችና ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የተሰጡት ማብራሪያዎች በቂ ማሳያዎች ናቸው። በቀሪው ጊዜም ይህን መሰል ገንቢና አስተማሪ ዐሳቦችን በሚገባ በማንሸራሸር በተቋም ደረጃ መፍትሔ የሚፈለግበትን መንገድ በመጠቆም በጉባኤው ላይ የተነሡ ዐሳቦችን መሠረት በማድረግ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ የሚያርፍበትን ሁኔ ታ በማመቻቸት ቢያንስ በዚህ ዓመት ችግሮቻችንን በውል ተገንዝበን ከችግሮችን መውጣት በመጀመር ቅድስት ቤተክርስቲያናችንን መታደግ እንድንጀምራለን የሚል ተስፋ አለን።

በአጠቃላይ በዘንድሮ ጉባኤያችን ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ጉባኤው መገባደጃ ቀን ድረስ የተመዘገቡ ውጤታማ ተግባራትን እውቅና መስጠት ተገቢ ስለሆነ ጉባኤው ያማረና የተሳካ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት ያደረጉት ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ዶ/ር የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒውዮርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ፣በልዩ ልዩ ኮሚቴዎች በመታቀፍ ውጤታማ ሥራ ላከናወናችሁ የኮሚቴ አባላት፣ለጉባኤው ሞገስ በመሆን ለሰነበታችሁ ለመላው ጉባኤ አባለት ምስጋና ሊቸራችሁ ይገባል።

ከሁሉ በላይ ዘመኑን የሚመጥን አባታዊ መልዕክት በማስተላለፍ፣ በጸሎት በመክፈትና በመዝጋት ፣አባታዊ ምክርና ትምህርት በመስጠት በትዕግሥት ጉባኤውን ሲመሩ የሰነበቱት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ቅድስት ጸሎትዎና ቡራኬዎ ለጉባኤያችን ሞገስ ሆኖታልና ዘወትር ቡራኬዎ እንዳይለየን እንጸልያለን።

“ልዑል እግዚአብሔር ጉባኤያችንን በሰላም ያስጨርሰን! ”

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
ጥቅምት ፱ ቀን ፳፻ ፲ወ ፮ዓ.ም
አዲስ አበባ -ኢትዮጵያ