ጥቅምት ፱ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
“””””””””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
***

ብፁዕ አቡነ ሙሴ የምዕራብ አውስትራሊያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በ፵፪ኛው ዓለም አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ የሀገረ ስብከታቸውን ሪፖርት አቅርበዋል።

ብፁዕነታቸው በሪፖርታቸው ባለፉት ሦስት ዓመታት በኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ባለመቻላቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤዎች ሳይሳተፉ መቅረታቸውን ገልጸው በቅርቡ ደግሞ ቋንቋና ፖለቲካን ምክንያት በማድረግ በሀገረ ስብከታችን በተፈጠረውን ችግር ምክንያት ምዕመናን እንዳይለያዩ በቅርበት ለመቆጣጠርና ምክር ለመስጠት በዚያ ለመቆየት ተገድጃለሁ ብለዋል።

በግንቦት 2015 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ ለስብሰባ መምጣታቸውን የገለጹት ብፁዕነታቸው በትግራይ ክልል በተፈጠረው ችግር ምክንያት በሀገረ ስብከታችን ስር በቆዩ ሦስት አብያተ ክርስቲያናትና በቅርቡ በእኛ ሥር የቆየን አንድ ቤተክርስቲያን ጨምረው በህገ ወጥ መንገድ ተሹመናል የሚሉ መነኮሳት ቋንቋና ፖለቲካን ምክንያት በማድረግ ወስደዋቸዋል ብለዋል።

አሁን የተወሰዱት አብያተ ክርስቲያናት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥር ይተዳደሩ የነበሩ መሆናቸውን የገለጹት ብፁዕነታቸው ቅዱስ ሲኖዶስ መተዳደሪያ ወይም መመሪያ በማዘጋጀት ተቋማዊ ሕልውናቸው እንዲረጋገጥ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

በሀገረ ስብከታቸው በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደነበር የገለጹት ብፁዕ አቡነ ሙሴ በዚያው አገር ተወልደው ያደጉ 45ዲያቆናትና 4 ቀሳውስትን ለማዕረገ ክህነት ማብቃታቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ጊዜ በሀገረ ስብከታቸው ሥር የሚገኙ ምዕመናን ለሁለት ተከፍለው እንደሚገኙ በሪፖርታቸው የገለጹት ብፁዕነታቸው ግማሾቹ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እና ከቅዱስ ሲንዶስ ጋር መሆናቸውን በመግለጽ ላይ የሚገኙ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ ተለይተናል በማለት ከህገ ወጥ ተሿሚዎቹ ጋር ወግነዋል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በውጭ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ችግር እየተፈጠረ ስለሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ ወጥ የሆነ መመሪያ በማጣትና አህጉረ ስብከቱ ለሚገኙባቸው መንግሥታት በማሳወቅ ችግሩን ከመሰረቱ ሊፈታው ይገባል በማለትም ሪፖርታቸውን አጠቃለዋል።

በመጨረሻም ብፁዕነታቸው በአውስትራሊያ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥር የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በየ ዓመቱ እንደሚደረገው ሁሉ ለሰበካ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ ገቢ የሚደረግ ገንዘብ እንዲልኩልኝ በተደጋጋሚ ያቀረብከት ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ ባለመቻሉ ከግል ገንዘቤ ለበረከት የሚሆን ሁለት ሺህ የአሜሪካ ዶላር ገቢ አድርጌያለሁ ብለዋል።