ኅዳር ፳፬ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
“””””””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
——————-
የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን አስመልክቶ የጋራ የውይይት መድረክ እንዲመቻችና በሚደረገው ውይይትም ችግሮችን በዝርዝር በመለየትና በመፈተሸ የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንዲቻል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባኤ ጥቅምት ፳፯ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል።
ይህንን መሰረት በማድረግም ኅዳር ፲፰ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም በተደረገው የጋራ ውይይት እንደ ችግር ተለይተው በቀረቡ ዋና ዋና ነጥቦች ዙሪያ ሰፊ ውይይት በማድረግ መግባባት ላይ መደረሱን ተከትሎ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሔኖክ በውይይቱ ወቅት ተለይተው የተገለጹትን ችግሮች በማስመልከት በሰጡት የማጠቃለያ ሀሳብ” የመልካም አስተዳደር ችግሮቹ ተለይተውና ተቆጥረው ይሰጡን እኛም ችግሮቹን ፈተንና ቆጥረን እናስረክባለን” በማለት በገቡት ቃል መነሻ ነት አስተዳደር ጉባኤው ኅዳር ፳፬ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም ባደረገው ልዩ ስብሰባ በ፲፪ ነጥቦች የተለዩት የመልካም አስተዳር ችግሮች በመሸኛ ደብዳቤ ለሀገረ ስብከቱ እንዲሉኩ የወሰነ ሲሆን የውሳኔ አፈጻጸሙን በተመለከተም ሦስት የመምሪያ ኃላፊዎች ተከታትለው እንዲያስፈጽሙና ስለ አፈጻጸሙም ሪፖርት እንዲያቀርቡ መድቧል።
የጠቅላይ ቤተክህነቱ ፍላጎት ሕግ፣ደንብና መመሪያ ተከብሮ እንዲሰራ፣ፍትህ እንዲነግስ፣ደሀ እንዳይበደል፣ በሲኖዶስ ውሳኔ በጸደቀውና ለሀገረ ስብከቱ በተሰጠው ደንብ መሰረት ብቻ ሥራዎች እንዲሰሩ እንጂ ሌላ ፍላጎት እንደሌለው ጉባኤው ገልጾ ህጉንና ለሀገረ ስብከቱ የተሰጠውን ደንብ በማክበር መሥራት እስከተቻለ ድረስ በጋራና በስምምነት ለአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን እድገት ለመስራት ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኑን በአጽንኦት ገልጿል።
በመጨረሻም ጉባኤው አንዳንድ ወገኖቾ ይህንን ሕግ፣ ደንብና መመሪን አክብሮና አስከብሮ ለመስራት የቀረበን ተቋማዊ ጥሪ ያልተፈለገ ቅርጽና ትርጉም በመስጠት የሀገረ ስብከቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዳይፈቱ በተለያዩ መንገዶች የሚያደርጉት ጥረት ከግርግር ለማትረፍ እንጂ ለቤተክርስቲያን በመቆርቆር እንዳልሆነ በግልጽ የሚታወቅ ስለሆነ ከአድራጎታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ብሏል።