ጥር ፲፬ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
————————-

የከተራ፣የጥምቀትና የቃና ዘገሊላ በዓላት በራያ አላማጣና በስድስቱ ወረዳዎች በታላቅ መንፈሳዊ ሥነሥርዓት ተከብሮ መዋሉን የሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት በላከልን ዘገባ ገለጸ።ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ተወልደው ባደጉበት ራያ አላማጣ ከተማ ከሦስት ዓመታት በኋላ በዓላቱን እንዳከበሩ የገለጸው የሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት ሕዝበ ክርስቲያኑ በነቂስ በመውጣት በዓሉም ፍጹም ሰላማዊና ደማቅ በሆነ መልኩ ማክበሩን ገልጿል።

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረው ጦርነት ካቆመ በኋላ በድምቀት በተከበረው በዓል ላይ የተገኙት ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ችግሮቹ ሁሉ ተወግደው ሰላማዊ በዓል ለማክበር ያበቃን ልዑል እግዚአብሔር ምስጋና ይገባዋል ካሉ በኋላ ያገኘነውን ሰላም በመጠበቅና በመንከባከብ የተቸገሩ ወገኖቻችንን በመርዳትና በመደገፍ በዓሉን ልናከብረው ይገባል በማለት አታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ብፁዕነታቸው ከዚሁ ጎን ለጎን በአላማጣ ከተማ በዓይነቱና በስፋቱ ልዩ የሆነውን የአላማጣ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ለማሰራት የመሰረት ድንጋይ አኑረዋል፤አዲስ የሚሰራውን የአላማጣ ቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያንን ሕንጻ ቤተክርስቲያን ጎብኝተው ለተሰበው ሕዝበ ክርስቲያንም የማጽናኛ ትምህርት፣ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተዋል።

በአላማጣ አካባቢ በሚገኘው የራያ ባላ ወረዳ ምሥራቀ ጸሐይ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያንና በአምስት የገጠር አብያተክርስቲያናት ሐዋርያዊ ጉዞ በማድረግም ሕዝበ ክርስቲያኑን በማጽናናትና በማስተማር አባታዊ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የሰጡ ሲሆን የተሰሩ የልማት ሥራዎችንም በመጎብኘት አባታዊ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል።ብፁዕነታቸው ሐዋርያዊ ጉዞ ባደረጉበት ቦታ ሁሉ ሕዝበ ክርስቲያኑ በነቂስ በመውጣት ደማቅ አቀባበል አድርጎላቸዋል ሲል የሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት በላከልን ዘገባ ገልጿል።