በዓሉ በተለይ በጀርመን ሔሰን ግዛት ፍራንክፈርት ከተማና አካባቢው ያሉ አራት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በጥምረት በደብረ ኀይል ቅዱስ ዑራኤል ወቅዱስ ያሬድ ቤ/ክ አዘጋጅነት ጥር ፲፪ ቀን የ፳፻፲ወ፮ ዓ.ም ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ የጀርመንና አካባቢው እና የምሥራቅ ጎጃም አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት በማኅሌት በቅዳሴ ሥርዓተ ጥምቀቱን በመፈጸም በድምቀት ተከብሮ ውሏል ።

በተመሳሳይ በዚያው በሀገረ ጀርመን ባየርን ግዛት ደቡብ ጀርመን ወረዳ ቤተ ክህነት ሥር የሚገኙ ሦስት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በዚሁ ዕለት በጥምረት ኾነው በጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ቤ/ክ አዘጋጅነት በድምቀት አክብረዋል ።

እንደዚሁም በሀገረ ኔዘርላንድ ደግሞ በዕለተ ቀኑ ዓርብና ቀዳሚት ጥር ፲ እና ፲፩ በዓለ ከተራውና በዓለ ጥምቀቱ በሀገረ ኔዘርላንድ በ፫ት ጠቅላይ ግዛት የሚገኙ ሦስት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በኔዘርላንድ ሀገር ወረዳ ቤተ ክህነት አስተባባሪነትና በተረኛው ደብር በአምስተርዳም ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክ አዘጋጅነት በኖርዝ ሆላንድ ጠቅላይ ግዛት በአምስቴልፌን ከተማ በጥምረት የተካሄደው የከተራና የጥምቀት በዓል አከባበር አንዱ ነው ።
ክብረ በዓሉም በኢትዮጵያዊው ቅዱስ ትውፊት መሠረት በምድረ አውሮፓ በሀገረ ኔዘርላንድ ዐሥራ ኹለቱም ጠቅላይ ግዛት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ምእመናንና ምእመናት በአንድ ላይ ተሰባስበው የቃል ኪዳኑ ታቦታት ወደ ባሕረ ጥምቀት ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት በተረኛው ደብር ቤተ መቅድስ ተገናኝተው ዋዜማ ከተቆመ በኋላ በካህናት ከብረው በሕዝበ ክርስቲያኑ ታጅበው ከቅጠረ ቤተ ክርስቲያን ወጥተው ወደ ባሕረ ጥምቀት በመሔድ በዚያ እንዲያድሩና ሥርዓተ ቅዳሴውንም በመንፈቀ ሌሊት እንዲከናወን ተደርጎ በዕለተ ቀኑም ጠዋት የባሕረ ጥምቀት ተባርኮ ንዝኀተ ማይ ከተፈጸመ በኋላ በመጡበት አኳኋን የመልስ ጉዙ በማድረግ በታላቅ ኦርቶዶክሳዊ ሥነ ሥርዓት በልዩ ኹኔታ እጅግ ላቅ ባለ በድምቀት ተከናውኗል ።
ይኽ የበዓለ ጥምቀት በሀገረ ኔዘርላንድ በዚህ መልኩ ሲከበር ዘንድሮ ለኹለተኛ ጊዜ ሲኾን የበዓሉም አከባበር በከተማው ማዘጋጃ ቤት ዕውቅና አግኝቶና ፈቃድ ሰጥቶት ታቦታተ ሕጉ የሚጓዙበት የከተማው መንገድ ተዘግቶ የተከናወነ በዓል ነው ። በበዓሉም ላይ የአምስተርዳም የአብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ተወካይና ሌሎችም እንግዶች ተገኝተዋል። እንግዶቹም በዚህ ልዩ በኾነ በዓለ ጥምቀት ላይ በመሳተፋቸው የተሰማቸውን ታላቅ ደስታ ገልጸዋል። የከተማው ጋዜጣም የዜና ሽፋን ሰጥቶታል።

በኹሉም አካባቢዎች የአየሩ ኹኔታ ከዜሮ በታች እስከ -፲ ዲግሪ ሴንቲግሬድ ደርሶ በጣም ቢቀዘቅዝም የወረዳ አብያተ ክህነት ሥራ አስኪያጆችና የየክፍሉ ሓላፊዎች ፣ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ፣ የሰንበት ት/ቤት መዘምራንና ብዙ ምእመናንና ምእመናት በተገኙበት በማኅሌት ፣ በቅዳሴ ፣ በትምህርት ፣ በመዝሙር በደመቀ ኹኔታ ተከብሮ ውሏል።

የተቀሩት አብያተ ክርስቲያናትም በየአጥቢያቸው በዓሉን በድምቀት አክብረዋል።ሲል ሀገረ ስብከቱ በላከልን ዘገባ ገልጿል።