ጥር ፳፫ ቀን ፳፻፲ወ፮ ዓ/ም
******
አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ
“””””””””””””””””””””

በ፲፰፻፺ወ፰ ዓ/ም በንጉሠ ነገሥት አጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የተመሠረተውና ፻፲፰ ዓመታት ያስቆጠረው ሕንጻ ቤተመቅደስ በእድሜ ርዝመት ምክንያት በመጎዳቱ ምክንያት ለመንፈሳዊ አገልግሎት አመቺ በሆነ መንገድ እድሳት ተደርጎለት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ተባርኮ መንፈሳዊ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

በቡራኬ ሁለት ዓመታት የቆየው የእድሳት ሥራ ተጠናቆ በቅዱስ አባታችን የቡራኬ ጸሎት አገልግሎት ሲጀምር ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ፮ አበው ሊቃነ ጳጳሳት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የመምሪያ ኃላፊዎች፣ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎች፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ምእመናንና ምእመናት ተገኝተዋል።

የሕንጻ ቤተክርስቲያኑ እድሳት የውጪና የውስጥ ግድግዳ እድሳት፣ የሳንቃና የመስኮት እድሳት፣ የቅዱሳት ሥዕላት እድሳት፣ የጣሪያና የወለል እድሳትና ሌሎች ሥራዎችንም እንደሚጨምር የገዳሙ አስተዳዳሪ ጸባቴ አባ ወልደማርያም አድማሱ ገልጸዋል። ጸባቴ ጨምረውም ሕንጻው ጥንታዊ ከመሆኑ አንጻር እድሳቱ ከፍተኛ ጥንቃቄ የተደረገበት መሆኑን ገልጸዋል።

የቡራኬ በዓሉ ቀጥሎ በነገው እለት ታቦታቱ ወጥተው ሕዝቡን በመባረክ ቅዳሴ ቤቱ እንደሚከበር በመርሐ ግብሩ ላይ ተገልጿል።