በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የኢሉ አባ ቦራ ሀገረ ስብከት የአመራሩን የማስፈጸም ብቃት ለመጨመርና ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት ያለመ ስልጠና ለ5 ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ ቆይቷል። ስልጠናው የአማራሩን ክፍተት ለመሙላት ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት የሚተገበረውን መሪ ዕቅድ ለማስፈጸም አቅም ለመፍጠር ተብሎ የተዘጋጀ መሆኑ ተነግሯል።
ይህ ስልጠና የተዘጋጀው የወረዳ አመራርና የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች የማስፈጸም ብቃት ለመጨመር ታልሞ ሲሆን ከዓላማ አንጻር የታሰበው ሁሉ ተሳክቷል።ባለፉት 5 ቀናት ስልጠናውን ሲከታተሉ የነበሩ አንዳንድ ሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት ተቋሙን ለማጠናከር ታስቦ የተሰጠው ይህ ስልጠና እስካሁን ያልተለመደ ሆኖ ሀገረ ስብከታችን ይህን ዓይነት ዕድል ፈጥሮ እንድንሰለጥንና እንድንሻሻል ማድረጉ በለውጥ ጎዳና ላይ መገኘቱን ያሳያል ብለዋል።
በዚህ ስልጠና ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው ለሰልጣኞች የሥራ መመርያና የምስክር ወረቀት የሰጡት የኢሉ አባ ቦራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባልና የመቱ ፈለገ ሕይወት የሥነ መለኮት መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ጠባቂ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ዶ/ር እንደተናገሩት ስልጠናው ያለንበት ደረጀ ያሳየንና ለሚፈለገው ለውጥ ራሳችንን እንድናዘጋጅ ያደረገ በመሆኑ ከስልጠናው ባገኛችሁት ዕውቀት ቀጣይ በትጋት እንድትሠሩ ታስቦ ዕድሉን አመቻችተናል ብለዋል።
ስልጠናው በሀገረ ስብከቱ ሕዝብ ግኑኝነት መምርያ ከመቱ ማዕከል ማኅበረ ቅዱሳን ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን የስልጠናውን ሙሉ ወጭ የመቱ ማዕከል ማኅበረ ቅዱሳን ሸፍኗል።
ዘገባው የሀገረ ስብከቱ ሕዝብ ግንኙነት ነው