በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት እንዲሁም በመላው ዓለም የምትገኙ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምዕመናን ወምዕመናት እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ በሰላም አደረሳችሁ አሸጋገራችሁ
“ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ ወይጸግቡ ጠላተ ገዳም – በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፥ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል” መዝ ፡ ፷፬ ( ፷፭ ) ፥ ፲፩
ከላይ የተገለጸው ኃይለ ቃል የአምላካችንን ድንቅ መጋቢነት የሚገልጽ ሲሆን፤ እግዚአብሔር አምላካችን ዓመታትን በቸርነቱ እየለወጠ፤ የበረከት እጁን ሳያጥፍ እየመገበ፤ የሰዎችን ማንነት ሳይለይ ለክፉም ለደጉም፤ ለኃጥኡም ለጻድቁም፣ ለድሀውም ለሀብታሙም፣ ለአሕዛብም ለሕዝብም የምሕረት ዝናቡን እያወረደ ፍጥረትን በሙሉ የሚያረካ አምላክ እርሱ ብቻ መሆኑን ያስረዳናል። እንዲሁም ሥነ-ፍጥረትን ብንመረምር የበጋና የክረምት መፈራረቅ፤ ተራሮች በዝናብ መርካታቸው፤ ከድርቀት (ከፀሐይ) ወራት በኋላ የሚመጡት የበረከት (የዝናብ) ጊዜያት እንዴት ባለ በሚያስደንቅ ሁኔታ የምድሪቱን ገጽታ እንደሚቀይር እንገነዘባለን።
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን
አሮጌው ዘመን አልፎ አዲሱ ዘመን ሲተካ በምን ዓይነት መንፈስ ነው የምንቀበለው ለሚለው ጥያቄ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ምላሽ ይሰጠናል። «የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት፤ በመዳራት እና በሥጋ ምኞት፣ በስካርም፣ በዘፈንም፣ ያለልክም በመጠጣት፣ ነውርም ባለበት፣ በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና» በማለት ያስተምረናል። (1ጴጥ.፬፥፫) ዘመናትን በቸርነቱ የሚያሳልፈው እግዚአብሔር ነው፡፡ በተሰጠን የአንድ ቀን ዕድሜ ኖሬበታለሁ? ብለን ራሳችንን ልንመረምር ይገባል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በኃጢአት የኖርበትን ዘመን በሕይወት እንዳልኖርበት ነግሮናል፡፡ ለምን ቢባል በደሙ የከበርን ክርስቲያኖች አምላካችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስለን ባለመገኘታችን ነው፡፡
በክርስቶስ ክርስቲያን ተሰኝተን በጥምቀት ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ተወልደን የማይጠፋውን ልጅነት ካገኘን በኋላ መጠመቃችንን የክርስትና መጨረሻ አድርገን በመውሰድ በስም ብቻ ክርስቲያኖች በመባል በክፋት ጸንተን እንገኛለን፡፡ ሥራ የሌለው እምነት ፣ፍሬ የሌላት በለስ ሆነን ከመገኘት ክርስትናን ኖረንበት ልናልፍ ይገባል፡፡
እግዚአብሔር በቸርነቱ ዘመንን ያቀዳጀን በመንፈሳዊ ሕይወት ታድሰን ተለውጠን አዲስ የተሻለ መንፈሳዊ ሰው እንድንሆን ነው። አዲስ ሰው መሆን ማለት ያለፈ ዘመንን ክፉ ግብር/ሥራ/ መተው፣ ደግሞም ኃጢአት ላለመስራት መታቀብና ራስን መግዛት ነው።እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ለመጨረሸዋ የፍርድ ቀን መልካምን ቃል የሚያሰማንን ተግባር ለማከናወን ለመልካም ሥራ መነሳሳት፣ የመንፈስ ፍሬያትን ማፍራት ያስፈልጋል። «የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት ነው።» ገላ፭፥ ፳፪
“እነሆ የመዳን ቀን አሁን ነው።” (፪ኛ ቆሮ ፮፥፪) ባሳለፍነው ዓመት በሀገራችን ብሎም በዓለማችን እጅግ በጣም ብዙ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ክስተቶችን አሳልፈናል። ለአብነትም ያኽል በሰሜኑ እንዲሁም በተለየዩ በሀገራችን ክፍሎች እጅግ በጣም ብዙ ንጹሐን ሕይወታቸውን አጥተዋል ፣ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል ፣ ብዙ ሕጻናት ወላጅ አልባ ሆነዋል። ምንም በማያውቁት እጅግ በጣም ብዙ ንጹሐን የጦርነት ሰለባ ሲሆኑ ተመልክተን አዝነናል። እንዲሁም በተፈጥሯዊ ክስተት ደግሞ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በተለይም በሰሜኑ እና በደቡቡ የሀገራችን ክፍል በመሬት መንሸራተት ምክንያት ብዙ ወገኖቻችን ለሞት ፣ ለከፍተኛ የአካል ጉዳት እንዲሁም ቀላል ለማይባል ለኢኮኖሚያዊ ፣ ለማኅበራዊ እና ለስነ-ልቦናዊ ጉዳት እንደተዳረጉ እንገነዘባለን።
በዚህ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ቀውስ ምክያንት ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን እግዚአብሔር አምላካችን ሐገረ ሕይወትን መንግስተ ሰማያትን እንዲያወርስልን ፣ ከቤት ንብረታችሁ ተፈናቅላችሁ ላላችሁ አምላካችን በሰላም ወደመንደራችሁ እንዲመልሳችሁ ፣ ቤተሰቦቻችሁን በሞት አጥታችሁ ላላችሁ ልጆቻችን መጽናናቱን እንዲልክላችኹ ሰላም ላጡ ሁሉ ሰላማቸውን እንዲመልስላቸው የዘወትር ጸሎታችን ነው።
በዘመነ ማቴዎስ እጅግ በጣም ብዙ የበደሉንን ይቅር ብለን ፣ የበደልናቸውን ክሰን ፣ ለሰው ሁሉ ፍቅርን ሰጥተን ፣ ፍቅርን በመቀበል ፣ የፍቅር አምላክ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልጆች መሆናችንን በግልጥ የምናሳይበት የፍቅር ፣ የሰላም ፣ የደስታ ፣ የጤና ፣ የበረከትና የመተሳሰብ ፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለጥፋት ፣ ሕዝቡ ለስደት የማይዳረግበት ዘመን ይሆንልን ዘንድ እንዲሁም ከኃጢአታችን በንስሐ ውኃ የምንታጠብበት፣ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለእኛ በቀራንዮ የቆረሰልንን ቅዱስ ሥጋውን የምንበላበት፣ ያፈሰሰልንን ክቡር ደሙን የምንጠጣበት ዘመን እንዲሆንልን እግዚአብሔር አምላካችንን በጸሎት ልንለምን ይገባል።
“እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
አባ ገሪማ
የጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል