መስከረም 2/2017 ዓ.ም

በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በመንበረ ጵጵስና ወናጎ ወረዳ ቤተክህነት ሥር በሚገኘው በወናጎ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ወቅዱስ ዮሐንስ ቤተክርስቲያን  የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በዓለ እረፍቱ የመንበረ ጵጵስና ወናጎ ወረዳ ቤክህነት ዋና ፀሐፊ ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ እሸቱ ዋለ የሁለቱ አብያተክርስቲያናት ዋና አስተዳዳሪ መልአከ ጽዮን ቀሲስ ግሩም በቀለ የሁለቱ ቤተ መቅደስ ስብከተ ወንጌል ኃላፊ ሊቀ ስዩማን ቀሲስ ምሕረቴ ገብረ ሥላሴ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን የአድባራት አስተዳዳሪዎች የነገ ቤተክርስቲያን ተረካቢ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች የወናጎና ከዙሪያው ከሚገኙ ወረዳዎች ቁጥራቸው ብዙ የሆነ ምዕመናን በተገኙበት በታላቅ መንፈሳዊ ክብርና ድምቀት ተከብሯል።

መርሐ ግብሩን ዲያቆን ወንዳየሁ ተረፈ  የመሩ ሲሆን  #የዕለቱን ወንጌል ያስተማሩት የመንበረ ጵጵስና ወናጎ ወረዳ ቤክህነት ዋና ፀሐፊ ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ እሸቱ ዋለ  ሲሆኑ  መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ስለእውነት ክርስቶስ ኖሮና መስክሮ  ያለፈ ሐዋርያ ነው፡፡ መሆኑን  “ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን አግብቶ ነበርና በእርስዋ ምክንያት ራሱ ልኮ ዮሐንስን አስይዞ በወኅኒ አሳስሮት ነበር፤ ዮሐንስ ሄሮድስን። የወንድምህ ሚስት ለአንተ ልትሆን አልተፈቀደም ይለው ነበርና።”(የማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ ፮:፲፯)

በዚህም ምክንያት በወኀኒ አሳስሮት ነበር፡፡እርሱም እውነትን መናገር አላቆመም ነበር፡፡” በበሩ አደባባይ የሚገሥጸውን ጠሉ፥ እውነትም የሚናገረውን ተጸየፉ። ” (ትንቢተ አሞጽ 5:10) የተባለውን ትንቢት በእርሱ ተተገበረ መሆኑን በመግለጽ

በመጨረሻም እንዲህ ሆነ፦ “ወዲያውም ንጉሡ ባለ ወግ ልኮ ራሱን እንዲያመጣ አዘዘው። ሄዶም በወኅኒ ራሱን ቈረጠ፥ ራሱንም በወጭት አምጥቶ ለብላቴናይቱ ሰጣት፥ ብላቴናይቱም ለእናትዋ ሰጠች። ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው መጡ በድኑንም ወስደው ቀበሩት።”(የማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ ፮:፵፯)  ከቅዱሳት መጽሐፍት የቅዱስ ዮሐንስን ክብር በመግለጥ በሰፊው ትምህርት ሰጥተዋል።

በመጨረሻም ለቤተክርስቲያን የልማት ሥራዎች የማስተባበር ሥራ ተከናውኖ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል።

መረጃውን ያደረሰን ሀገረ ስብከቱ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ነው።