መስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም (ሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት)
=============================

የወልድያ ከተማ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ትናንት መስከረም 1 ቀን የዘመን መለወጫ በዓልን በማስመልከት ለሀገረ ስብከቱ ብፁዓን አባቶች የእንኳን አደረሳችሁ መርሐ ግብር አካሂዷል። ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት በመርሐ ግብሩ ለተገኙ የሰንበት ት/ቤት አባላት አባታዊ መልእክትና የአገልግሎት መመሪያ አስተላልፈዋል። ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ የሰንበት ትምህርት ቤቶችን ለማጠናከር የደከሙት ድካም ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሱት ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የብፁዕነታቸውን ህልም ለማሳካት ሀገረ ስብከቱ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አብራርተዋል።

መሪ እቅዱ ለይስሙላ ሳይኾን በትክክል ተግባራዊ እንዲሆን ሰንበት ትምህርት ቤቶችን የሚያጠናክር የሐዲሳት መጻሕፍት ትርጓሜ መምህር የሀገረ ስብከቱ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ ክፍል ኀላፊ አድርጎ ከመመደብ ባሻገር 5 አሠልጣኝ መምህራን በጠቅላይ ቤተክህነት መሠልጠናቸውንና ሥርዐተ ትምህርቱን ለመተግበር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ብፁዕነታቸው ተናግረዋል። የሀገረ ስብከቱና የወረዳዎች የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ለሚስተዋሉ ክፍቶች የመፍትሒ አካል እንድሆኑና አባላቱም እንዲያግዟቸው አሳስበዋል። ትልቁ ሥራችን ሰው ማትረፍ ነውና ኹላችንም የጋራ ሥራ ሠርተን፥ የጋራ ውጤት ማምጣት አለብን ያሉት ብፁዕነታቸው በበዓላት ከመዘመር ባለፈ መሠረተ ሃይማኖት ላይ በማተኮር በእምነትም በምግባርም መጠንከርና ስለሚዘመረው ጉዳይም በቂ እውቀት ሊኖረን ይገባል ብለዋል።

ክርስትናችንን ማስፋት የምንችለው መሠረተ እምነቱን ማወቅ ስንችል ነው ያሉት ብፁዕነታቸው የጸሎተ ሃይማኖትን 12 ቱን አንቀጾች መያዝና ማብራራት መቻል፣ በትምህርተ ሃይማኖት፥ በነገረ ቅዱሳን፣ በምሥጢረ ሥላሴና በምሥጢረ ሥጋዌ ትውልድን ለመቅረጽ መዘጋጀት እንዳለባቸው አባታዊ መመሪያ አስተላልፈዋል። መረጃውን ያደረሰን የሀገረ ስብከቱ ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ነው።