መስከረም 5/2017 ዓ/ም
=======================
በመረሐ ግብሩ ላይ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ጥበባት ሞላልኝ መርጊያ፣የሀገረ ስብከቱ ም/ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሃይማኖት ነጻነት አክለወግ፣የሀዋሳና ዙሪያ ወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ላዕከ ወንጌል ደግፌ ባንቡራ፣የሀገረ ስብከቱ የየመምሪያ ኃላፊዎችና ልዩ ልዩ ሠራተኞች፣የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣የገዳማትና የአድባራት ም/ሊቃነ መናብርትና ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች የተገኙ ሲሆን መርሐ ግብሩ በብፁዕነታቸው ጸሎት ተጀምሯል።

– በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያሬዳዊ ዜማና ቅኔ ቀርቧል።
– በመቀጠልም የሲዳማ ሀገረ ስብከት የአድባራትና የገዳማት አስተዳዳሪዎችና ተወካዮች የእንኳን አደረሰዎ መልእክታቸውን ለብፁዕነታቸው አስተላልፈዋል።
– የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ጥበባት ሞላልኝ መርጊያም ብፁዕነታቸውን እንኳን አደረሰዎ በማለት ያለፈው 2016 ዓ/ም እንደ ሀገረ ስብከት ስኬታማ ነን።

በብፁዕነታቸው መመሪያ ሰጭነትና አርቆ አሳቢነት በተለይ በስብከተ ወንጌል ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል። ለአብነት ያህል ሀገረ ስብከት አቀፍ ጉባኤ ከርእሰ ከተማው እስከ ወረዳ ከተማዎች በማዘጋጀት የሲዳማ አፎ( ቋንቋ) ሰባክያንን በማሠማራት፣ በዚህ አዳዲስ አማንያን በብዛት መጠመቅ፣የብያተ ክርስቲያናት መስፋፋት፣አሁን ያረፍንበት መንበረ ጵጵስና በአጭር ጊዜ ተሠርቶ ብፁዓን አባቶች በተገኙበት ተመርቆ ሥራ ላይ መዋል፣በፍጥነት እየተገነባ ያለው ሎጎስ ሕንጻ እና የመሳሰሉት የተሠሩበት ዓመት በመሆኑ ስኬታማ ነን ማለት እንድንችል አድርጎናል። ለዚህም ትልቁ ድርሻ የብፁዕ አባታችን በመሆኑ በድጋሚ ብፁዕ አባታችንን እንኳን አደረስዎ ብላችሁ አመስግኑልኝ በማለት ሀሳባቸውን አጠቃልለዋል።

በመጨረሻም ብፁዕ አባታችን አቡነ ዮሴፍ በክቡር ሥራ አስኪያጁ እንደተገለጠው በ2016 ዓ/ም በእናንተ በጋራ ትብብር ብዙ ሥራዎች ተሠርተዋል። እንደምሳሌ ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ ዓመት እያከበርንበት ያለው መንበረ ጵጵስና ዛሬ እንሥራው ብንል አንችልም። ምክንያቱም ትናንት ዛሬ ስላልሆነ። ስለዚህ ዛሬም መሥራት ያለብንን ካልሠራን ነገ ሌላ ቀን ነው።ለነገ ዛሬ መሥራትን መልመድ አለብን።

ሌላው ከሀገረ ስብከት ጀምሮ እስከ አጥቢያ ያለ አገልጋይ ከሕዝቡ ጋር መግባባት ያስፈለጋል። ስህተትም ከተፈጠረ ዝም ብሎ ከማለፍ ይልቅ ማረም ያስፈልጋል። ነህምያን መሆን አለብን ነህምያ የፈረሰውን ለመገንባት ወገኖቹን ያበረታታ ነበር። ዛሬም በመካከላችን ብዙ የፈረሱ ነገሮች ስላሉ ተመልሰው እንዲገነቡ መሥራት ከካህናት ይጠበቃል።መሪዎች እንደመሆናችን እንደ ሰሎሞን አስተዋይ መሆን ያስፈልጋል። ካልሆነ ይህን ዓለም ቀድመን መምራት አንችልም።

በአጠቃላይ እግዚአብሔርን ካስቀደምን በጸሎት ከጸናን እግዚአብሔርም ከእኛ ጋር ከሆነ ይህን የመከራ ጊዜ ማለፍ እንችላለን ለዚህ ግን ማንበብ መጠየቅ ራስን ማብቃት መሠረታዊ ጉዳይ ነው። በጥቅሉ ዘመኑን የሰላም የፍቅር የበረከት ዘመን ያድርግላችሁ የሚል አባታዊ መልእክት አስተላልፈው በብፁዕነታቸው ጸሎትና ቡራኬ የፕሮግራሙ ፍጻሜ ሆኗል።

መረጃው የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሕዝብ ግንኙነት ነው