መስከረም ፲፫ ቀን ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም
“””””””””””””””””””””””””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
*****

የጠቅላይ ቤተ ክህነት ስራ አስኪያጅ እና የባህርዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም በበኩላቸው በዓሉ ፍጹም ደማቅ እና ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር የከተማ አስተዳደሩ እያደረገ ላለው ስራ አመስግነው የደመራ በዓል በታቀደው መንገድ ሰላማችንን እና አንድነታችንን በሚገልፅ መልኩ ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ምዕመኑ ከጸጥታ አካላት ጋር በትብብር እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል::

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል::

በውይይት መድረኩ ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በዓሉ ምንም የጸጥታ ስጋት ሳይኖር እንዲከበር ፖሊስ በአዲስ አበባ ካሉ አድባራት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ገልጸው በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ፖሊስ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርጎ ማጠናቀቁን ገልጸዋል::

የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው የመስቀል ደመራ በዓል ኃይማኖታዊ ትውፊቱን እና ሰላማችንን በሚገልፅ መልኩ እንዲከበር ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ስናደርግ ቆይተናል ያሉ ሲሆን በቀጣይም ትኩረት በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ በትብብር በመስራት የከተማችን አንዱ ድምቀት የሆነው የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርገን አጠናቅቀናል ብለዋል::

© አዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን።