“የመስቀል እንቅፋት ተወግዶአል” ገላትያ ፭፥፲፩

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን !!
“የመስቀል እንቅፋት ተወግዶአል” ገላትያ ፭፥፲፩

በሀገር ውስጥ እና በውጭ ዓለም የምትኖሩ የተከበራችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ምዕመናን እና ምዕመናት!!
በቅድሚያ እንኳን እግዚአብሔር ለ ፳፻፲፯ ዓ/ም በዓለ መስቀል በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ አደረሰን!!
የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ጥላቻ የክርስቲያኖች መገለጫ ባሕርይ አይደለም፤ እና ጌታ ሰላምን እና ዕርቅን ያደርግ ዘንድ ጥልን በመስቀሉ ገደለ።ኤፌ ፪ ፥፲፭-፲፮።
በዚህም ጌታ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ባሳየን የፍቅር ጥግ ባደረገልንም ዕርቅ እና ሰላም ምክንያት መስቀሉ፦
– የሰላም
– የፍቅር
– የዕርቅ ምልክት ሆነ።

በዚህም የሰላም ምልክት ቅዱስ መስቀል ታዲያ ብዙዎቹ ከሕመማቸው እየተፈወሱ ሰላምን ያገኙ ነበር። ነገር ግን ይህ የጌታችን እና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መስቀል፦
– ሙታንን እያስነሣ
– ለምጻሙን እያነጻ
– ጎባጣውን እያቀና
– ሕሙማንን እየፈወሰ
ተአምራትን ሲሰራ ይህ እውነት ያልተዋጠላቸው አይሁድ በመስቀሉ ላይ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ሥራ ቀብረው ለመደበቅ ሰይጣናዊ ሐሳብ በልባቸው ገባ ስለዚህ መስቀሉን ቀብረው ከ፫፻ ዓመታት በላይ ተራራ ሆኖ ገዝፎ አስኪታይ ድረስ ከአካባቢያቸው ያለውን ቆሻሻ እና የቤታቸው ጥራጊ ወስደው ደፉበት፤ ዛሬም በዚህ መንገድ እውነትን በማይሹ ወገኖች ለሀገር በረከት የሆኑ በርካታ እውነቶች እንዲህ ይቀበራሉ። ነገር ግን እግዚአብሔር ሥራውን የሚሰራበት የእግዚአብሔር የሥራ ጊዜ የሚሠራበት የእግዚአብሔር የሥራ ጊዜ ሲደርስ እነ ኪራኮስ እውነት ያለችበትን ስፍራ መደበቅ አይችሉም። ምክንያቱም ለሀገር እና ለወገን የሚጠቅሙ በርካታ የተደበቁ እውነቶችን ፈልፍለው የሚያወጡ እነ እሌኒን እግዚአብሔር በጊዜው ጊዜ ይቀሰቅሳልና።ቅዱስ መስቀል ከተቀበረበት ሥፍራ የተገኘበትን በዓል ስናከብርም እውነቱ ሁሉ ይህ ነው።

እግዚአብሔር አምላክም መስቀሉን ከተቀበረበት ስፍራ እንድታወጣ ለዚህ ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ዓላማ ያዘጋጃት ንግሥት እሌኒ በሰጠችው መመሪያ መሠረት ደመራ ተደምሮ በእሳት ተለኩሶ ሰንድሮስ የተባለ ብዙ ዕጣን ተጨምሮበት የዕጣኑ ጢስ የጌታ መስቀል ከተቀበረበት ስፍራ ጎልጎታ ላይ አረፈ። ሰገደ ጢስ በጎልጎታ እንዳለ ሊቁ።

ደመራው ተለኩሶ የዕጣኑ ጢስ ካረፈበት ቦታ ላይ መስቀሉ ያለበት ሥፍራ ተገኝቷልና መስከረም ፲፯ ቀን ቁፋሮ ተጀምሮ መጋቢት ፲ ቀን ቅዱስ መስቀል እንደ ፀሐይ እያበራ ከተቀበረበት ሥፍራ ወጣ። ቀደዌ እስራት የነበሩ በርካታ ሕሙማንም በመስቀሉ ላይ በተገለጠው የሆነኘ በእግዚአብሔር መለኮታዊ ኃይል ከሕመማቸው ተፈወሱ። እንዲህ የሚፈውሰውን ቅዱሱን መስቀል ለፈውስ ያልታደለው የአይሁድ ሕዝብ ተባብሮ ቀበረው። ነገር ግን በእግዚአብሔር ድንቅ ጥበብ የመስቀሉ እንቅፋት ተወገደ፤ መስቀሉ ወደ አደባባይ ወጣ። ወደ ኢትዮጵያም መጣ። እኛም ዛሬ ለዓላማችና ለአንድነታችን እንቅፋት የሆኑብንን የየጀሮች የሆኑብንን ነገሮች እግዚአብሔር እንዲያስወግዶን እውነት ተባብረው የሚቀብሩ አይሁድን ሳይሆን ትውልድ የሚፈወስበትን  እውነትን ቆፍረው የሚያወጡ እነ እሌኒን ልንሆን ይገባል።

የተወደዳችሁ ክርስቲያኖች !!
የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን የእግዚአብሔር ኃይል ነው። ፩ኛ ቆሮንቶስ ፩፥ ፲፰
በአሉን ስናከብር ኃይልን በሚሰጠን በክርስቶስ
– የታረዙትን በማልበስ
– የተራቡትን በማጉረስ
– የተጠሙትን በማርካት እና የተቸገሩትን በመርዳት መሆን እንዳለበት በእግዚአብሔር ልዩ ፍቅር ልናሳስባችሁ እንወዳለን። መስቀሉ ክርስቶስ ፍቅሩን ለእኛ ያሳየበት የፍቅር ምልክት ነውና በዓሉን ስናከብር በፍቅር ሊሆን ይገባል። መስቀሉ ክርስቶስ ሰላምን ለሰው ልጆች የሰጠበት የሰላም አርማ ክርስቶስ እኛን ከራሱ ጋር ያስታረቀበት የዕርቅ ምልክት ነውና የተጣላን ታርቀን በወንድማማች መዋደድ በዓሉን ልናከብር ይገባል።

በማጠቃለያም እንደ ምሥራቅ ሐረርጌ እና እንደ ሐረር ከተማ የሚመለከታችሁ የመንግስት አካላት ብሎም በሌላ የእምነት ተቋም ውስጥ ያላችሁ የተከበራችሁ ወገኖቻችን ይህ የመስቀል ደመራ በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱም ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ በተባበሩት መንግስታት በትምህርት በሳይንስ እና ባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ)ከማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል እንደመመዝገቡ መጠን የጋራ በዓላችን፤የጋራ ታሪካችን፤የጋራ ቅርሳችን፤የጋራ ውበት እና ድምቀታችን እንዲሁም የአንድነታችን መገለጫ እንደመሆኑ መጠን ለበዓሉ ድምቀት የበኩላችሁን ሚና እንድትወጡ በእግዚአብሔር ስም እያሳሰብን በዓሉ የሰላም በዓል እንዲያደርግልን እንመኛለን።

ልዑል እግዚአብሔር ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ሰላሙን ለሕዝቦቿ ፍቅር እና አንድነትን ይስጥልን!!
አባ ኒቆዲሞስ
የምሥራቅ ሐረርጌ ሀ/ስብከት ጳጳስ
እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል
መስከረም ፲፭ ፳፻፲፯ ዓ/ም