“ወወሀብኮሙ ትእምርተ ለእለ ይፈርሁከ ከመ ያምስጡ እምገጸ ቀስት – ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ ፥ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው”

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ_አሐዱ አምላክ አሜን!!!

እጅግ የምንወዳችሁ እና የምናከብራችሁ በሀገረ ስብከታችን ፣ በመላው ዓለም የምትገኙ ክርስቶሳውያን ውድ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን እንኳን ለ2017 ዓ.ም የቅዱስ መስቀል የደመራ በዓል በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ!
“ወወሀብኮሙ ትእምርተ ለእለ ይፈርሁከ ከመ ያምስጡ እምገጸ ቀስት – ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ ፥ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው”
መዝ 59፥4
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከምታከብራቸው ከዘጠኙ ንዑሳን በዓላት አንዱ ይህ የቅዱስ መስቀል የደመራ በዓል ነው። ደመራ የሚለው ቃል ደመረ፣ ጨመረ፣ አንድ አደረገ፤ ከሚለው የግእዝ ቃል የመጣ ሲሆን የሚገልጸው ደግሞ መቀላቀልን፣ መገናኘትን፣ መሰብሰብን፣ መጣመርን፣ መዋሐድን በአጠቃላይ ሱታፌን፣ አንድነትን እና ኅብረትን ነው። ቅዱስ መስቀሉ የተገኘበት በዓልም ስለሆነም ደመራ እንጨቶች የሚደመሩበት የበዓለ መስቀል ዋዜማ ነው።

ይህን በዓል የምናከብርበት ምክንያት አይሁድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል የተለያዩ ገቢረ ተዓምራትን ሲያደርግ በመመልከታቸው በቅናት ተነሳስተው ቀብረውታል ቦታውንም የቆሻሻ መጣያ አድርገው ቆይተዋል። ኋላም የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት በሆነችው ንግሥት ኅሌኒ አማካኝነት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መስቀል ከተቀበረበት እንደወጣ ከመጽሐፈ ስንክሳራችን እንረዳለን።
መስቀል የሰላማችንና የድኅነታችን የመቀደሳችን ዓርማ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጆች ለማዳን፥ የዘላለም ሕይወትን ለመስጠት መስዋዕትነት የከፈለበት ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ያፈሰሰበት መንበር፥ ሲሆን አምላካችንን የምንመለከትበት መስታወት ነው።

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ “መስቀሉ ለወልድ ለነፍስየ ፀወና – የወልድ መስቀል የነፍሴ መጠጊያዋ ነው” ይላል። ይህ ማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ መስቀሉ ስላደረገልን የማዳን ሥራ ሲያስረዳን ነው።
ለእኛ ለክርስቲያኖች ቅዱስ መስቀል ኃይላችን ፣ ቤዛችን ፣ ምልክታችን ፣ መጠጊያችን. . ነው። ስለዚህ ይህንን የቅዱስ መስቀል በዓል ስናከብር ታላቅ መንፈሳዊነት በተመላ መልኩ ሊሆን ይገባል። በቅዱስ መስቀሉ የተደረገልን ዕርቅ ፣ ሰላም ፣ ድኅነት ፣ ዕድገት… ነው። እኛም ይህንን በዓል ስናከብር አምላካችን ያደረገልንን ማዳን እያሰብን ፣ በአፋችን የሰላምን መዝሙር እየዘመርን ፣ ይቅር እየተባባልን ፣ የተቸገሩትን እየረዳን መልካም ነገሮችን በሙሉ በማድረግ በመንፈሳዊ ስርዓት ልናከብር ይገባል።

ወቅታትን ፣ ዓመታትን ፣ አዝማናትን እንደየስርዓቱ የሚያፈራርቅ ፥ ፍጥረታትን የሚመግብ የቸርነት እና የይቅርታ ባለቤት አዲሱን ዓመት የተባረከ ዘመን ያድርግን። ከቅዱስ መስቀሉ ረድዔት በረከት ያሳትፈን።

እግዚአብሔር ሀገራችንን ይባርክልን
አባ ገሪማ
የጌዴኦ ኮሬ ቡርጂ ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል