እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ በሰላም አሸጋግሮ ለበዓለ መስቀሉ አደረሳችሁ አደረሰን፡፡

የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ርእሰ ከተማ በሆነችው በደሴ ከተማ ሆጤ መስቀል አደባባይ ጌታችን መድኃኔታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ክቡር መስቀሉ የተገኘበት በዓል አረጋዊውና አንጋፋው ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ የደቡብ ወሎና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የከሚሴ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣ የሀገረ ስብከቱ የየክፍል ኃላፊዎች፣ የደሴ ከተማ አስተዳደር ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅና የክፍል ኃላፊዎች፣ የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት የመንግሥት ኃላፊዎች፣ እንዲሁም የከተማዋ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከበረ፡፡

በበዓሉም በደሴ ከተማ አድባራት ሊቃውንት መሰቀል አብርሃ በከዋክብት፤ እምኩሉሰ ፀሐየ አራየ የሚለው ያሬዳዊ ዜማ የቀረበ ሲሆን በመቀጠልም ከሁሉም አድባራት በተውጣጡ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ይቤሎሙ ኢየሱስ ለአይሁድ እመኑ ብየ ወእመኑ በአቡየ ፤ አበርህ በመስቀልየ ፡ እመኑ ብየ የሚለው ለዘብ ቀርቧል፡፡

በመቀጠል በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ወወሀብኮሙ ትዕምርተ ለእለ ይፈርሁከ (ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሀቸው ከጠላት ዲያብሎስ ያመልጡበት ዘንድ) በሚል የትምህርት ርእስ ሰፊ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተው መላው ሕዝበ ክርስቲያን በግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም በመገኘት የመስቀሉን በዓል እንድናከብ በማለት አስተላልፈዋል፡፡

ባጠቃላይ በርካታ መንፈሳዊና ማኅበራዊ መልዕክቶች የተላለፉ ሲሆን
የደሴ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ቃሲም አበራ እንጨቶች ተሰባስበው ችቦን፣ ችቦዎች ተሰባስበው ደመራን እንደሚፈጥሩ ሁሉ እኛም የተለያየ ሃይማኖትና ባህል ይዘን በአንድ ላይ በመተባበርና በመደጋገፍ አገራችንን ልናለማ ይገባል በማለት መልእክት ከስተላለፉ በኋላ ብፁዕ አባታችን አቡነ አትናቴዎስ ቃለ ምዕዳን ሰጥተው ደመራውን ባርከው በመለኮስ በዓሉ በሰላም ተጠናቋል፡፡

መረጃው የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ሕዝብ ግንኙነት ክፍል ነው ፡፡