ሐምሌ 15 ቀን 2017 ዓ.ም.

በመንፈስ ቅዱስ ጥሪ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት አንብሮተ እድ ሐምሌ 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ከተሾሙ ጳጳሳት መካከል ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል አንዱ ናቸው።

ብፁዕነታቸው በዋና ሥራ አስኪያጅነት ሲመሩት ለነበረውና ለመጀመሪያ ጊዜ በስሙ ጳጳስ ለሚሾምለት ጋምቤላ ሀገረ ስብከት የተቀቡ እና ቅዱስ ሲኖዶስ በጠረፋማ ስፍራ የሚያሳዩትን መልካም አፈጻጸም ተመልክቶ ተጨማሪ ስድስት አህጉረ ስብከትን በመጨመር በኀላፊነት ሰጥቷቸዋል።

ብፁዕነታቸው በሁሉም አህጉረ ስብከታቸው ተወዳጅ፣ ተናፋቂና በስስት የሚመለከቷቸው እንዲሁም በሁሉም ማኅበረሰብ ዘንድ ከበሬታን ያተረፉ በመሆናቸው ከዕረቡ ሐምሌ 9 ቀን 2017ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሐምሌ 13 ቀን 2017ዓ.ም. ድረስ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በዝማሬ፣ በወንጌል አገልግሎት ፣በምግባረ ሰናይና በተለያዩ ሁኔታዎች ሲከበር ቆይቶ ዛሬ በአሶሳ ሀገረ ስብከት በእንዚ መካነ ገነት መድኀኔዓለም ወደብረ ማርቆስ ካቴድራል ክቡራን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት የሥራ ኀላፊዎች የአሶሳ ሀገረ ስብከት የሥራ ኀላፊዎች፣ የአሶሳ ክልል መሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በተላቅ ድምቀት ተከብሮ ማጠቃለያውን አግኝቷል።

ይህ በዓለ ሢመት ከወትሮው ለየት የሚያደረግ ከሥጋዊ ድግስ ወደ መንፈሳዊ ድግስ ያደላ በመሆኑና ለብዙዎች ነፍስ መዳን ምክንያት ለመሆን የወንጌል አገልግሎትን ያዘጋጀ መሆኑ ነው።

ብፁዕነታቸው በበዓለ ሢመቱ ሲገልፁ ይህ ሢመት የእኔ ሳይሆን የቤተክርስቲያን ነው። በመሆኑም ሀሴት ማድረግ ያለባቸው የቤተክርስቲያን አካላት ናቸው። ለዚህም የደስታቸው ምንጭ እንዲሆን ወንጌል ይሰበክ፣ መዝሙር ይዘመር ያመኑ ሁሉ እየመጡ ሲጠመቁ በሰማይ መላእክት ዘንድ ታላቅ ደስታ ይሆናል ብለዋል።

ብፁዕነታቸው ከወንጌል አገልግሎት ባሻገር በክልሉ አረንጓዴ አሻራቸውን በማኖር በዓለ ሢመታቸውን አክብረዋል። ችግኞችን ስለ መትከልና መንከባከብ የሰውልጅ የመጀሪያ ሥራው መሆኑን በማውሳት ይህንን የጥንተ ተፈጥሯ ኀላፊነት ተግባራዊ ማድረግ አዲሱን ትውልድ ማስጠለል መቻል ነው ብለዋል።
የበዓለ ሢመቱን ማጠቃለያ በማዘጋጀት የአንበሳውን ድርሻ የወሰደው የአሶሳ ሀገረ ስብከት እድለኛ ሆነን ይህንን በማክበራችን ደስተኞች ነን በማለት ገልፀዋል።

በመጨረሻም ልዩ ልዩ በጎ ስጦታዎች ተበርክተው የበዓሉ ፍፃሜ ሆኗል።