ኅዳር 6/2016 ዓ/ም ጭሮ
===
በብፁዕ አቡነ እንጦንስ የምዕራብ ሐረርጌና የአፋር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የሚመራው ጉባኤ በዛሬውም ዕለት የተጠናቀቀ ሲሆን በጉባኤው መዝጊያ ላይ የዞኑ የሃይማኖቶች ሕብረት የሥራ ሂደት መሪ ኃላፊ የሆኑት አቶ አወል …. ተገኝተው ስለወቅታዊው የዞናችን ሰላምና ጸጥታ ፣ እንዲሁም ተቻችሎ ስለመኖር ፣ የሃይማኖት ተቋማት የሰላም አምባሳደር በመሆናቸው ስለ ሰላም ጠንክረው መሥራትና ማስተማር እንዳለባቸዉ አጽንኦት ሰጥተው ያሳሰቡ ሲሆን ፣ በተለያዩ የከተማና የገጠር አብያተ ክርስቲያናት በተለያዩ ወረዳዎች በሚገኙ በመሬት አስተዳደርና በከተማ አስተዳደር በኩል እየደረሰባቸው የሚገኘውን አስተዳደራዊ በደል ለአቶ አወል ከተለያዩ የወረዳ ቤተ ክህነት ኃላፊዎች ፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎችና ምክትል ሊቃነ መናብርት መፍትሔ እንዲሰጣቸው ችግሮቹን ነቅሰው ያቀረቡ ሲሆን እንደ ሃይማኖቶች ሕብረት የሥራ ሂደት ኃላፊነታቸው ይህን ችግር ከሀገረ ስብከቱ ጋር በመሆን ለሚመለከተው ክፍል አሳውቀው መፍትሔ እንደሚያሰጡ ገልጸዋል።

በመቀጠልም ጉባኤው ባለ 14 ነጥብ የጋራ አቋም መግለጫ ያለው ቃለ ጉባኤ በመጋቤ ሥርዓት ቀሲስ ዘነበ ብርሃኑ የሀገረ ስብከቱ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ ከቀረበ በኋላ በ2015 የበጀት ዓመት በተለያዩ የሥራ ዘርፎች በመልካም አስተዳደር፣ በስብከተ ወንጌል ማስፋፋት ፣ የሰንበት ትምህርት ቤትን በማጠናከር ፣ ራስ አገዝ ልማትን በማፋጠን ፣ ወዘተ … ጥሩ የሥራ ውጤት ላስመዘገቡ የወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶችና የገዳማትና አድባራት ጽ/ቤቶች ከ1-3 ለወጡ የሰርተፍኬትና የተለያዩ የማጠናከሪያ ሽልማቶች ከብፁዕነታቸው የተቀበሉ ሲሆን ፣እንዲሁም ጥር 27/2015 ዓ/ም በተፈጠረው የቤተ ክርስቲያን ፈተና ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጎን በመቆም በሕግ በኩል መብቷን አስጠብቀው ከሕገወጡ ዘረፋ ለታደጉ 4 የበጎ ፈቃደኞች የሕግ ባሙያዎች ያበረከቱት አስተዋጾ በክቡር ሥራ አስኪያጁ በሊቀ ኅሩያን ቆሞስ አባ ፍቅረ ዮሐንስ ብርሃኑ ለጉባኤው ታዳሚ ሰፊ ገለጻ ከአደረጉ በኋላ የዕውቅና ሰርተፍኬትና የምስጋና ሽልማት ከብፁዕነታቸው እጅ ተቀብለዋል።

በመጨረሻም በብፁዕ አቡነ እንጦንስ የምዕራብ ሐረርጌና የአፋር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የጉባኤው ፍጻሜ ሆኗል ሲል የሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት በላከልን ዘገባ ገልጿል።