ጷጉሜን ፬ ቀን ፪፻፲፮ ዓ.ም.
__________

የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ “አዲሱን ዓመት በመንፈስ ዝግጅት እንቀበል” በሚል መሪ ቃል በጽርሐ ተዋሕዶ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ታላቅ መንፈሳዊ ጉባኤ አዘጋጀ።
ጉባኤው ከጠዋቱ 2:30 ላይ የተጀመረ ሲሆን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፀዕ አቡነ አብርሃም፣ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣ የምዕራብ ሐረጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ ፣ የአዊ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቶማስ፣ የሲዳማ ሀገረ ስብከትና የታቦር ፍኖተ ጥበብ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፣ የማዕከላዊ ጎንደር ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ፣ የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ዋና ኀላፊ ክቡር መልአከ ሰላም አባ ቃለጽቅ ሙሉ ጌታ (ዶ/ር) የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የየመምሪያ ኀላፊዎች፣ሠራተኞች እና የአዲስ አበባ ማዕከል የማኅበረ ቅዱሳን ዘማርያን እንዲሁም የፍኖተ ጽድቅ ማኅበር ዘማርያን በተገኙበት ተካሂዷል።

በመርሐግብሩ መጀመሪያ ላይ የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ካህናት መምሪያ ኃላፊ ክቡር ሊቀ ካህናት እንቖባሕርይ ተከስተ የሬዳዊ ዜማ ያቀረቡ ሲሆን በመቀጠልም የማኅበረ ቅዱሳን አዲስአበባ ማዕከል ዘማርያን ዝማሬ አቅርበዋል የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ አዲሱን ዓመት በአዲስ መንፈስ ለመቀበል የጋራ ጸሎትና ትምህርት እንዲኖር በማሰብ ያዘጋጀው ሲሆን ዋና ዓላማው በእምነት ፣ በንቃትና በተጋት ተሻግሮ አዲሱን የቸርነቱን ስጦታ ለመቀበል እንድንችል ማንቃት መሆኑን የመምሪያው ዋና ኀላፊ ገልጸዋል። አዲሱን ዓመት በአዲስ ሕይወት ፍትሕና ርትዕ የሰፈነበት አገልግሎት እንዲኖረን ለማስታወስ የተዘጋጀ መርሐግብር መሆኑን ኀላፊው አክለው ገልጸዋል። በመቀጠልም የመምሪያው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የመግቢያ ንግግር ሲያደርጉ በመሪ ቃሉ የተጠቀሰውን ቃል ከማብራራት ጀምረዋል። “መንፈስ” ስንል በምስጢራዊ ፍች ሲፈታ “ቅን ልቡና” ማለታችን ነው ብለዋል። በመንፈስ መታደስ ማለት አዲስ ቁሳቁስ መግዛት ሳይሆን ልብን ማደስ ማለት ነው ብለዋል። አዲሱን ዓመት የዓለም ሐሳብ ባላጣመመው በቅን ልቦና ልንቀበለው ይገባል የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።

በመቀጠልም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፀዕ አቡነ አብርሃም የተዘጋጀው መርሐግብር ያሳለፍነውን ዓመት በመዳሰስ የወደፊቱን በአዲስ መንፈስ እንድንቀበል የሚያነቃ መሆኑን በመግለጽ ከመጽሐፍ ቀዱስ ሁለት ጥቅሶችን በማንሳት ያለፈውን ጊዜ ለማዘከር የሚመጣውን ለማቀድ እንዲቻል አስትመረዋል። ለነቢዩ ዮናስ የተሰጠውን አምላካዊ ትዕዛዝ “ወደ ታላቂቱ ከተማ ሂደህ ስበክ” የሚለውንና የጌታችንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ትምርህት “ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው አንተ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥት ስበክ” የሚለውን በማንሳት ይህንን አምላክዊ መመሪያ በማክበር በአዲሱ ዓመት ስብከትን የዘወትር ሥራችን እንዲሆን መክረዋል። በአዲሱ ዓመት አይደለም ጥቅማጥቅም አንገታችን ለቤተክርስቲያን መስጠት መገለጫችን ነውና በርትተን ይህንን ማስቀጠል ይኖርብናል ብለዋል።

በመቀጠለም የሲዳማ ሀገረ ስብከትና የታቦር ፍኖተ ጥበብ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሊቀ ጳጳስ #ካለፈው_ዓመት_ተምረን_መጪውን_ዓመት_በመንፈስ_እንቀበል በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል። ጥናቱ ከ14 በላይ ርዕሰ አንቀፆች ያሉት ሲሆን አጽንዖት የተሰጠባቸውን ዋና ዋናዎቹን በማንሳት አብራርተዋል ። የብሔር ግጭት ፣ ጥላቻ ፣ የሰላም እጦት፣ የአስተዳደር ድክመት፣ የባሕል መቀወስ ፣ ፍትሕን ማስከበር አለ መቻል፣ የአንድነትን ስብራት መጠገን አለመቻል እና መሰል ነገሮችን በማንሳት ባሳለፍነው ዘመን ያለፉብን መሆኑን ጠቅሰው ለውጥ ማምጣት እንድንችል ግን ለችግሮች ሁሉ መፍትሔ በመስጠት እና የቤተክርስቲያን አንድነትን አስጠብቀን አዲሱን ዓመት መቀበል እንዳለብን አሳስበዋል። ከጥናቱ በመቀጠል የፍኖተ ጽድቅ መንፈሳዊ ማኅበር ዘማርያን ዝማሬ አቅርበዋል ።

በመጨረሻም በስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ማርቆስ የነገይቱን ቤተክርስቲያን አፅዕንዖት ሰጥተን እንድነሠራ ማሳሰቢያ ተሰጥቶ ቃለ ምዕዳን እና ቡራኬ ተደርጎ የጉባኤው ፍጻሜ ሆኗል።