ልጅ ያሬድ የተባለውን ግለሰብ በህግ ለመጠየቅ የሚያስችል ሥራ እየተሰራ ነው።

ነሐሴ ፳፮ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም
*******
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
******

ባለፉት ቀናት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ውስጥ በመግባት ከእምነቷ ውጭ የሆነ መዝሙር የዘመረች ወጣት የፈጸመችው ተግባር ጥፋት መሆኑን አምና በፈጸመችው ጥፋት በመጸጸት በቅድስት ቤተ ክርሰቲያን አውደ ምህረት ተገኝታ ይቅርታ መጠየቋን ተከትሎ ልጅ ያሬድ የተባለ ግለሰብ እንኳን የኃይማኖት ሀገር በሆነችው ኢትዮጵያ ቀርቶ እምነት የለሽ በሚባሉት ሀገራት የማይደረግ የድፍረት ስድብና አጋንታዊ የሆነ ጸያፍ ቃላትን በመጠቀም በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ በማህበራዊ ድህረ ገጹ ላይ በተደጋጋሚ ያስተላለፈውን መልዕክት ተመልክተነዋል።

በዚህ ድፍረት የተሞላበት ድርጊትም በርካታ ኦርቶዶክሳውያን አዝነዋል፣አልቅሰዋል፣ በድርጊቱ ክፉኛ በመበሳጨትም ከፍትህ አደባባይ ፍርድ እንደሚጠብቁ በተለያየ መልኩ እያሳወቁ ናቸው።

ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስን መስቀል ሁሌ መሸከም የየዕለት ተግባሯ ቢሆንም ከ፷ሚሊዮን በላይ ተከታይ ያላትንና ላለፉት ሁለት ሺህ ዘመናት ሀገርን በፍቅርና በስነምግባር ጥላ ሥር ሰብስባ ያኖረች ቤተ ክርስቲያን መሆንዋ እየታወቀ በእንዲህ አይነት በወረዳና ተሰምቶ በማያውቅ ድፍረት ቤተክርስቲያንን በመስደብ ሕዝበክርስቲያኑን ለማሳዘን መሞከር እጅግ አደገኛ ተግባር ነው።

ቤተክርስቲያንም ይህን ጸያፍ ተግባር የፈጸመና የተሳደበን ግለሰብ በዝምታ ማለፍ ስለማይገባት ጉዳዩን በህግ መምርያ በኩል በመከታተል ተገቢውን ሁሉ የምታደርግ መሆኑን ከወዲሁ እየገለጸች በህግ መምሪያችንና በህግ ባለሙያዎቻችን አማካኝነት አስፈላጊውን ሁሉ እስክታደርግ ድረስ ምዕመናን ከቅድስት ቤተክርስቲያን የተማራችሁትን ትዕግስትና ትህትናን መሰረት ባደረገ አግባብ በፍጹም ክርስቲያናዊ ጨዋነት እንድትጠብቁና በጉዳዩ ዙሪያ ከጸጥታ ከአካላት ጋር በትብብርና በአንድነት በመጠቆም እንድትተባሩ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ጥሪዋን ታስተላልፋለች።