በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
•ብፁዕ አቡነ አብርሃም
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳርና የሰሜን ጐጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
•ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
•ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤
ዓመቱን ጠብቆ ስለ አጠቃላይ ተልእኮአችን ለመወያየት በዚህ ጉባኤ የሰበሰበን አምላካችን ስሙ የተመሰገነ ይሁን፤
“ወይእዜኒ ግብኡ ኀበ ኖላዊሃ ወዓቃቢሃ ለነፍስክሙ፤ አሁንም ወደ እረኛችሁና ወደ ነፍሳችሁ ጠባቂ ተመለሱ” (1 ጴጥ 2÷!5)
ሁሉን የሚችል አምላካችን እግዚአብሔር በፍቅሩና በፍቅሩ መነሻነት ብቻ ፍጥረታትን በሙሉ እንደፈጠረ ቅዱስ መጽሐፍ ያስተምረናል፤ ከፈጠረም በኋላ የክብሩ ተሳታፊ እንዲሆኑ ወዶ ክብሩን አድሎአቸዋል፡፡ እግዚአብሔር ለፍጡራኑ ካደላቸው ነገሮች አንዱ በየዓይነታቸው ጠባቂና መሪ እያደረገ በፍጡራን ላይ ፍጡራንን መሾሙ ነው፤ ይህ ስጦታ በሰማይም ሆነ በምድር ላሉ ፍጥረታት የተሰጠ የሱታፌ መለኮት ስጦታ ነው፡፡
ይህም በመሆኑ ሁሉም ፍጡራን አራዊትም ሆኑ እንስሳት ይብዛም ይነስ ጠባቂና መሪ እንዳላቸው እናስተውላለን፤ በተለይም የፍጥረታት ቁንጮ የሆኑ መላእክትና ሰዎች መሪና ሹም እንዳሏቸው የማንክደው ሓቅ ነው፡፡ ቅዱስ መጽሓፍም ይህንን ደጋግሞ ያስረዳል፤ የእነዚህ ሁሉ ላዕላዊ ጠባቂና መሪ ደግሞ እግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር በፍጡራን ላይ ፍጡራንን ጠባቂዎች አድርጎ ሲሾም ፍጡራንን የክብሩ ተሳታፊ ለማድረግ እንጂ የእሱ ጥበቃ አንሶ ወይም ድጋፍ ሽቶ አይደለም፡፡ ስለሆነም ፍጹምና ላዕላዊ የሆነ ጥበቃው ሁሉንም ያካለለ ነውና ከእሱ ቊጥጥርና ጥበቃ ውጭ አንድም ነገር እንደሌለ የምንስተው አይደለም ፡፡
•ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
•የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
በአምሳለ እግዚአብሔር በተፈጠረውና በክብር መልዕልተ ፍጡራን በሆነው ሰው ላይ በዚህ ዓለም የተሾሙ ሁለት አካላት አሉ፤ እነሱም የመንፈስና የዓለም መሪዎች ናቸው፡፡ በተለይም የመንፈስ መሪዎችና ጠባቂዎች የተባሉት በመንፈስ ቅዱስ ተሹመን በዚህ ክርስቶሳዊ ጉባኤ የተሰበሰብነው እኛ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ነን፡፡
ይህ ጉባኤ በሀገር ውስጥና በውጭ ለሚገኙና በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን መሪና ጠባቂ ነው፤ ከዚያም ባሻገር እንደ ቃሉ እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ ቃሉን በመስበክ ፍጥረተ ሰብእን በሙሉ የመጥራት ተልእኮ ለእኛ የተሰጠ የቤት ስራ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የተሰጠን ኃላፊነት እጅግ በጣም ታላቅ እንደመሆኑ የሚጠበቅብን ውጤትም በዚያው ልክ ትልቅ ነው፤ ብዙ ከተሰጠው ብዙ ይፈለግበታል ያለው የጌታችን አስተምህሮም ይህንን ያስታውሰናል፡፡
ሁላችን እንደምንገነዘበው አሁን የምንገኝበት ዘመን የጸላኤ ሠናያት መንፈስ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ከምንም ጊዜ በበለጠ ጦሩን ሰብቆ የተነሣበት ጊዜ ነው፤ አሁን ያለው ዓለም በሀገራችንም ሆነ በሌላው ክፍለ ዓለም ላሉ ኦርቶዶክሳውያን ከባድ ፈተና ደቅኖብናል፡፡ ክፉው መንፈስ የሰውን አእምሮ በማዛባት ምእመናንን በቅዱስ መጽሐፍና በሕገ ተፈጥሮ ከተመደበላቸው የጋብቻ ሕግ በማስወጣት እንስሳት እንኳ የማይፈጽሙት ነውረ ኃጢአት እንዲፈጽሙ በመገፋፋት ላይ ይገኛል፡፡ በአማንያን ልጆቻችን ላይም በረቀቀ ስልት ግድያ፣ እገታ፣ አፈና፣ የመብት ተጽዕኖ እና አድልዎ በማድረግ እንደዚሁም በአስመሳይ ስብከትና አምልኮ ጣዖትን በማለማመድ ሕዝቡ ሳይገባውና ሳይጠነቀቅ ከእግዚአብሔር መንግሥት እንዲወጣ እያደረገ ነው፡፡
•ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
•የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
ክፉው መንፈስ በተራቀቀና በተራዘመ ስልት ሊውጠን በተነሣ ልክ እኛም ከእሱ እጥፍ በሆነ መለኮታዊ ኃይል ልንመክተው ካልቻልን በፈጣሪም ሆነ በትውልድ እንደዚሁም በታሪክ ፊት በኃላፊነት መጠየቃችን አይቀርም፡፡ መከላከል የምንችለውም ችግሩን በውል ከመረዳት አንሥቶ ሕዝቡን በደምብ በማስተማርና በመጠበቅ እንደዚሁም ለመሪነታችን ዕንቅፋት ከሚሆኑን ዓለማዊ ነገሮች ራሳችንን በማራቅ ነው፡፡ ሕዝቡም በዚህ ዙሪያ ሊያደምጠንና ሊከተለን የሚችለው መስለን ሳይሆን ሆነን ስንገኝለት ነው፡፡ ሕዝቡ ሊከተለን የሚችለው እሱን በብቃት ለመጠበቅ ዓቅሙም ተነሣሽነቱም ቁርጠኝነቱም እንዳለን ሲመለከት፣ እንደዚሁም ከዕለት ተዕለት ተግባራችንና አኗኗራችን የሚያየው ተጨባጭ እውነታ ኅሊናውን ሲረታ እንደሆነ አንርሳ፡፡
የምናስተምረው ሌላ የምንሰራው ሌላ ከሆነ ግን ከሕዝቡ አእምሮ መውጣታችን እንደማይቀር መገንዘብ አለብን፤ በመሆኑም በሰብእናችን፣ በአስተዳደራችን፣ በአመራራችንና በጥበቃችን ሁሉ እንደቃሉና እንደቃሉ ብቻ ለመፈጸም መትጋትና በቁርጥ መነሣት ጊዜው አሁን ነው እንላለን፡፡ ይህ ሲሆን በምእመናንና በእኛ መካከል ያለው ግንኙነት አስተማማኝና እንከን የለሽ ይሆናል፤ ይህ ከሆነ እውነትም የመሪነት፣ የእረኝነትና የመልካም ተምሳሌነት ኃላፊነታችንን በትክክል ተወጥተናል ማለት እንችላለን፡፡
•ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
•የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
የሰው ልጆች በዚህ ዓለም ሲኖሩ የተሟላ ሰላምና ጣዕመ ሕይወት ሊኖራቸው የሚችለው በመንፈሳዊ ኑሮአቸው የተሻለ ነገር ስላገኙ ብቻ አይደለም፡፡ ሰዎች ከሥጋዊ ክዋኔም ጭምር የተፈጠሩ እንጂ እንደመላእክት ሥጋ የሌላቸው መንፈስ ስላይደሉ ለኑሮአቸውና ለሥጋዊ ክዋኔአቸው የሚሆን ነገር ያስፈልጋቸዋል፡፡ በዚህም ዓለማዊው አስተዳደር የተመቻቸ መደላድል ሊፈጥርላቸው ግድ ነው፤ ዓለማዊው አስተዳደርም የመለኮትን ተልእኮ ለመፈጸም የተሾመ ሹመኛ እንደመሆኑ የእግዚአብሔርን ሕዝብ በትክልል መምራት ይጠበቅበታል፡፡ ምንም ቢሆን የተቀበለው ኃላፊነት የእግዚአብሔር ነውና በሚሰራው ሁሉ በሿሚው አምላክ ከመጠየቅ አያመልጥም፡፡
እኛም በዚህ ዓለም የእግዚአብሔር ወኪሎች ስለሆንን ቢሰሙንም ባይሰሙንም ዓለማውያን ሹማምንትን የማስተማርና የመምከር ኃላፊነት አለብን፡፡ ይህ የሁለታችን ኃላፊነት እንደ እግዚብሔር ፈቃድ ስንፈጽም የሕዝብ ሰላምና በረከት፣ ፍቅና አንድነት፣ ዕድገትና ልማት በአስተማማኝ ሁኔታ ይረጋገጣል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ በሀገራችንም ሆነ በአካባቢያችን እየሆነ ያለው ይህ አይደለም፤ አለመግባባት በዝቶአል፣ ማኵረፍና መቀያየም ሰፍቶአል፤ ነገሩ ሁሉ ግራ የሚያጋባና የተመሰቃቀለ ሆኖ ይታያል፡፡
ችግሩ ከሕዝብ አልፎ የአምልኮ ስፍራዎችንና የአምልኮው ፈጻሚዎችን ዒላማ ያደረገ እግዚአብሔርን መዳፈር እየተለመደ መጥቶአል፤ ይህ ለአንድ ሀገር ወይም ሕዝብ የውድቀት ምክንያት ከሚሆን በቀር ከቶውኑም የዕድገት ምልክት ሊሆን አይችልም፡፡
ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ደግሞ ይህ ክፉ ድርጊት እየተፈጸመ ያለው በእኛው ልጆች በኢትዮጵያውያን መሆኑ ነው፤ ስለሆነም በከተማም፣ በጫካም፣ በገጠርም በየትኛውም ስፍራ የምትገኙ ልጆቻችን ምንም ይሁን ምን ሀገርንና ሕዝብን ከመጉዳት ተቆጠቡ፡፡ በተለይም ከቤተ ክርስቲያንና ከሀገር እንደዚሁም ሕዝቡን ከሚያገለግሉ ካህናትና ሲቪል ሰራተኞች እባካችሁ እጃችሁን አንሡ፤ ቤተ ክርስቲያን እኮ የእናንተና የሕዝቡ ሁሉ እናት ናት፤ በእናታችሁ ላይ መጨከንን እንዴት ተለማመዳችሁት? አሁንም ንስሐ ግቡ ያለፈው ይበቃል፡፡ ልብ በሉ ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት አይበጅም፤ ሰውን መጉዳትና እግዚአብሔርን መዳፈር አቁሙ፤ የእግዚአብሔር ገንዘብ የሆነውን ሥርዓተ አምልኮም ያለቦታው አታውሉ፤ ጥያቄአችሁን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዕድል ስጡ፡፡ በእግዚአብሔር ስም ለመላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንና ልጆቻችን የምናስተላፈው ወቅታዊ መልእክታችን ይህ ነው፡፡
በመጨረሻም በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሁለንተናዊ አገልግሎትና የስራ አፈጻጸም ላይ ለመምከርና ለመወሰን ኃላፊነት ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ በዛሬው ዕለት መደበኛና ዓመታዊ ጉባኤውን የጀመረ መሆኑን ለሕዝበ ክርስቲያኑ እናበስራለን፡፡
እግዚአብሔር ጉባኤያችንን ይባርክ!
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን::
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥቅምት ፲፪ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፤