ታኅሣሥ ፳፱ ቀን ፳፻ ፲፯ ዓ.ም

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

“የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ።” ፩ኛ ዮሐ ፫÷፱

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

ከሁሉ አስቀድሜ ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን በሰላምና በጤና በሕይወት ጠብቆ አሁን ላለንበት ጊዜና ሰዓት ስላደረሰን ስሙ የተመሰገነ ይሁን።

ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ምን ያህል እንደከበርን ሲናገር
“በልደቱ ተወለድነ ወበጥምቀቱ ተጠመቅነ ወከብረ በዝንቱ ሕሱር ሥጋነ ” በመወለዱ ተወለድን በመጠመቁም ተጠመቅን በዚህም የተዋረደው ሥጋችን ከበረ ይላል።

ክብር ይግባውና ጌታችንና አምላካችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ለአባታችን አዳም በገባው ቃል ካዳን መሠረት የሰው ልጅ ወደ ሚደነቅ ብርሃን ወጣ ጠላት ዲያብሎስ ላይፈታ ታሰረ ላይነሳ ወደ ሲኦል ረግረግ ተጣለ በስጋ ብዕሲ ተሰውሮ የሰውን ልጅ ድል የነሳውን ዲያብሎስን ክብር ይግባውና መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ “በከበረ በማርያም ማኅፀን ሥጋን ተዋሐድኩ” እንዳለ ሲራ ፳፬÷፲ እርሱም በሥጋ ብዕሲ በድንግል ማርያም ማኅፀን አድሮ ዲያብሎስን ድል አድርጎ የዘለዓለም ደስታና ረፍት ሰጠን

እንኳን ለ፳፻ ፲፯ ዓ.ም የጌታችንንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በሰላምና በጤና አደረሰን አደረሳቹ

ውድ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ኦርቶዶክሳውያን በወርቅ ወይም በብር በከበረ ዕንቁ ያይደለ በከበረ ደሙ ፈሳሽነት የገዛን መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ለዚህ ታላቅ በዓል ስላደረሰን ስሙ የተመሰገነ ይሁን እኛ ሰው መሆን አቅቶን ባለንበት ዘመን በማይደበዝዝ ፍቅሩ ሰው ሆኖ በሥጋ ማርያም ተገልጦ ፍቅሩን ያሳየን የወደደን ፈጣሪ ስሙ የተመሰገነ ይሁን።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ!

አባ በርተሎሜዎስ
የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ታኅሣሥ  ፳፱ ቀን ፳፻ ፲፯ ዓ.ም
መረጃውን ያገኘነው ከሀገረ ስብከቱ ምዞብ ግንኙነት ነው።