ማኅበረ ቅዱሳንና ሀገር አቀፍ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ያዘጋጁት የ2015 ዓ.ም የከፍተኛ ት/ተቋማት ገቢ ተማሪዎች ሽኝት መርሐ ግብር ተከናወነ።
ወደ ከፍተኛ ት/ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በሚከታተሉባቸው ጊዜያት ኦርቶዶክሳዊነታቸውን በማጠንከር እና በመንፈሳዊነታቸው በመበርታት ተምስጋኝ መሆን እንደሚገባቸው ብፁእ አቡነ ፊሊጶስ የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ሊቀ ጳጳስ ገልጸዋል።
ብፁእነታቸው ይህን የተናገሩት በ2015 ዓ.ም ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ማለፊያ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችን ለመሸኘት እና አደራ ለመስጠት በተዘጋጀ መርሐ ግብር ላይ በመገኘት ሲሆን መርሐ ግብሩ በማኅበረ ቅዱሳን እና በሀገር አቀፍ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት አማካኝነት የተዘጋጀ ነው።
የካቲት 11/2015 ዓ.ም በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ አዳራሽ በተዘጋጀው በዚህ መርሐ ግብር ላይ ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ የሆነ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በዕለቱ የተለያዩ መርሐ ግብሮች የቀረቡ ሲሆን ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ሁለት ተማሪዎች የላፕቶፕ ኮምፒዩተር ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።
እነዚህ ተማሪዎች ወደተመደቡባቸው ተቋማት ሲሄዱ ከትምህርታቸው ጎን ለጎን መንፈሳዊ ሕይወታቸውንም መርሳት እንደሌለባቸው የተገለጸ ሲሆን ማሳያ እንዲሆንም በተለያየ ጊዜ ከግቢ ጉባኤያት የተመረቁ እና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ አባላት ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ተደርጓል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የሀገር አቀፍ ሰ/ት/ቤቶች አንድነትን በመወከል ንግግር ያደረጉት ቀሲስ አርአያ እንዳሉት ተማሪዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር እያሉ በሰ/ት/ቤቶች ላይ ሲማሩ የነበሩትን መንፈሳዊ ሕይወት እና ቤተክርስቲያንን የማገልገል ልምድ ወደ ዩኒቨርስቲ ሲገቡም መርሳት እንደሌለባቸው ተናግረዋል።
በተጨማሪም የማኅበረ ቅዱሳን ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ግዛቸው ሲሳይ እንዳሉት ዛሬ ሽኝት የተደረገላቸው ተማሪዎች በሚሄዱባቸው የትምህርት ተቋማት ውስጥ ማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት አደራጅቶ የሚጠብቃቸው መሆኑን ገልጸው ከትምህርታቸው ጎን ለጎን መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ መበርታት እንደሚገባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
በመጨረሻም የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ምክትል ኃላፊ መልአከ ብርሃን ቀሲስ ተክለርትዕ ገብረ ወልድ የማደራጃውን መልእክት በማስተላለፍና ሁሉም አባላት በሚሄዱበት ሁሉ እግዚአብሔር አምላክ እንዲረዳቸው የሚማጸኑበት የጸሎት መጽሐፍ በመስጠት መርሐ ግብሩ ፍጻሜውን አግኝቷል።ሲል ማኅበሩ በላከልን ዘገባ ገልጿል።