የማኅበረ ቅዱሳን አዲስ አበባ ማእከል ለሚያስገነባው ባለ ዐስራ ሁለት ወለል ሕንጻ ገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም በግራንድ ኤልያና ሆቴል አካሂዷል። በመርሐ ግብሩ ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ(ዶ/ር)፣ የጅጅጋ ሱማሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ፣ የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ሙሉጌታ ስዩም(ዶ/ር)፣ የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ መምህር ዋሲሁን በላይ እና የአዲስ አበባ ማእከል ሰብሳቢ ዲ/ን ኃ/ማርያም መድኅን እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
የሚገነባው አዲሱ ሕንጻ ማእከሉ ወጣት የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችን በሙሉ አቅሙ በማስተማር የቤተ ክርስቲያን እና የሀገር ተረካቢ እንዲሆኑ ለማስቻል የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ እና በማእከሉ ለሚከናወኑ ልዩ ልዩ የሐዋርያዊ አገልግሎት፣ የሙያ አገልግሎት፣የሚዲያ ተደራሽነት እና ለቅዱሳት መካናት ተግባራት አቅም የሚፈጥር መሆኑ በዕለቱ ተገልጿል።
በመርሐ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒውዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) ለሁሉ ነገር መሠረት እና ለምንፈልገው ለውጥ የምርምር እና የትምህርት ተቋማት ያስፈልገናል ብለዋል፡፡ ብፁዕነታቸው አክለውም የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች ትልልቅ ተቋማትን ለማቋቋም የማንንም ርዳታ ሳንጠብቅ ዐሥር ሚልዮን የምንሆን ኦርቶዶክሳውያን በዓመት ውስጥ ባሉን የፆም ወቅቶች ብቻ ለቁርስ ወጪ የምናደርገውን ብናዋጣ ዓላማችንን ማሳካት እንችላለን ብለዋል፡፡
በመልዕክታቸው መጨረሻ ላይም ይህ የአዲስ አበባ ማእከል ሕንጻ የዚህ ስኬት አካል ስለሆነ ሁላችንም የድርሻችንን ብንወጣ በአንድ ዓመት ውስጥ መጨረስ እንችላለን በማለት ተናግረዋል።
የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም በበኩላቸው ይህ ዛሬ በአዲስ አበባ ማእከል እየተገነባ ያለው የወጣቶች ማእከል በአጠቃላይ ወጣቱ ትውልድ ስለ አገሩና ስለቤተ ክርስቲያኑ የሚመራመርበት፣ ዘመኑ ከሚያመጣቸው ፈተናዎች ተጠብቆ ለበጎ ነገር የሚነሳሳበት መሆኑን ተገንዝበን ምዕመናን ሁሉ ተረባርበን በአጭር ጊዜ ልናጠናቅቀው ይገባል በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ሰብሳቢው አክለውም ማኅበሩ ባለፉት 32 ዓመታት በሀገር ውስጥ እና በውጪ፣ በገጠርና በከተማ ውጤታማ ተግባራትን ማሳካት የቻለው በአባቶች ቡራኬ፣ በአባላቱ ጠንካራ ሥራ እና በምዕመናን ድጋፍ በመሆኑ ይህ ፕሮጀክት እንዲሳካ የሁሉም አካላት ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በዕለቱ በገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሩ ላይ ከተገኙት ታዳሚዎች 7,500,000.00 (ሰባት ሚሊዮን አምስት መቶ ሽህ ብር) ቃል የተገባ ሲሆን ለዚህ በጎ ዓላማ ምዕመናን ሁሉ እንዲሳተፉ የሕንጻ ግንባታ ኮሚቴው ጥሪውን አቅርቧል፡፡
© M.K