ሐምሌ ፲፱/፳፻፲፮ ዓ/ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በነገረ ድኅነት መሠረትነትና የዘለዓለማዊ ሕይወት ዋጋ ማግኛ እንዲሆኑ በዓላትን ታከብራለች።

በየዓመቱ ሐምሌ ፲፱ ቅዱስ ገብርኤል ክርስቲያን በመሆናቸው ብቻ በፈላው ውኃ ጋን ውስጥ እንዲጣሉ የተፈረደባቸውን ቅድስት ኢየሉጣንና ልጇን ቅዱስ ቂርቆስን ያዳነበት ዐቢይ በዓል በመሆኑ መታሰቢያቸው ባሉበት አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በድምቀት ይከበረል።

በዓሉ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአስኮ ደብረ ገነት ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ሲከበር ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ ሊቀ ትጉኃን ወንድወሰን የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ሊቀ ሊቃውንት አባ ኪዳነ ማርያም የካቴድራሉ አስተዳዳሪ፣ ሊቀ ኅሩያን ዮሐንስ ቀኖ የብፁዕነታቸው ልዩ ጸሐፊ፣ የሀገረ ስብከቱና የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት የሥራ ሓፊዎች፣ የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ በርካታ ምዕመናንና ምዕመናት ተገኝተውበታል።

በዓሉን አስመልክቶ በካቴድራሉ ሊቃውንት “ዘረዳዕኮሙ ለሰማዕት ወባላሕኮሙ እምእሳት ሊቀ መላእክት
እግዚኦ አድኅነነ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ እምዕለት እኪት” የሚለው ወረብ ቀርቧል።

በካቴድራሉ ሐመረ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራንም “ጥቡዕ ልቡ ለሕጻን የሚለውን አቡኑ ቃኝተውና ጸፍተው “ወዓዲ ከመ ኢይማስን ሥጋከ
ዲበ ሠረገላ ኤልያስ ህየ አነብረከ” የሚለውን አመላለስ ወረብ አቅርበዋል።

ትምህርተ ወንጌል በአማርኛ፣በኦሮምኛና በወላይትኛ ቋንቋዎች የተሰጠ ሲሆን በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት የሰጡት ሊቀ ትጉኃን ወንድወሰን የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ “ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፤” ፊልጵስዩስ ፩፥፳፱ በሚል ርእስ መነሻነት ስለቅድስት ኢየሉጣና ስለ ቅዱስ ቂርቆስ በመከራ ስለመጽናት እንዲሁም የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል እንዴት እንዳዳናቸው አስተምረዋል።

ሊቀ ትጉኃን በትምህርታቸው አክለውም እንደቅዱስ ቂርቆስ ለቤተሰቡ ለጎረቤቱ ለሀገር ለጓደኛው የመዳንና በእምነት የመጽናት ምክንያት የሚሆኑ ልጆች ለትውልዳችን እንደሚያስፈልጉ በምሳሌነት ገልጸዋል።

ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተዋል።

ብፁዕነታቸው የሰማዕታቱን የተጋድሎ ብዛትና የእምነት ጽና ከአሁኑ ዘመን ክርስትና ጋር በማነጻጸር አሳይተዋል።

እንደደመና የከበቡን ቅዱሳን ሰማዕታት በመከራ የታመኑላትን በእሳት ውስጥ ያለፉበትን ቅድስት እምነታችንን በመጠበቅ መንገዳቸውን ልንከተል ይገባል ብለዋል።

ዘመናችን ብዙ የሚያሳዝኑ ነገሮች የምንሰማበት ጊዜ ሆናል ያሉ ሲሆን በዚሁ ሳምንት በጎፋ ዞን በመሬት ናዳ ምክንያት በሞቱ ወገኖቻችን እጅግ አዝነናል ብለዋል።

ስለሆነም ወደ እጥዚአብሔር በመጮህ ከመጡብን መከራዎችና ተግዳሮቶች በላይ ሆነን በመጽናት ሰማዕታት መሆን ይገባናል ብለዋል።

በመጨረሻም ታቦታቱ ወደ መንበረ ክብራቸው የገቡ ሲሆን ጸሎተ ቅዳሴው በብፁዕነታቸው መሪነት ተከናውኖ ከቀኑ 9:00 ሰዓት የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል።©ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ