ሐምሌ ፫ቀን ፳፻ ፲ወ፭ዓ.ም
“”””””””””””””””””””””””””

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በክልል ትግራይ በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች ርዳታ ለመስጠትና በትግራይ ከሚገኙ አባቶች ጋር የተፈጠረው ችግር በውይይት ለመፍታት ዛሬ ፣ ሐምሌ ፫ቀን ፳፻ ፲ወ፭ዓ.ም ማለዳ መቐለ ከተማ ገብተዋል።

በቅዱስነታቸው የሚመራው የሰላም ልዑክ ቡድን መቐለ ሲደርስ በክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት አቀባበል የተደረገለት ሲሆን፤ በክልሉ ጽሕፈት ቤትም ከአቶ ጌታቸው ረዳ የጊዜያዊ መንግስቱ ርዕሰ መስተዳር ጋር ተወያይተው የሃያ ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርገዋል።

ቅዱስ ፓትርያርኩ ከክልሉ ጊዜያዊ መስተዳድር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ጋር በሰጡት የጋራ መግለጫ በትግራይ የሚገኙ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የተፈጠረውን ችግር ወደ ጠረጴዛ መጥተው በውይይት እንዲፈቱ አባታዊ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በዚሁ ጊዜ ቅዱስነታቸው እንደገለጹት ሁኔታው አስከፊ ቢሆንም የመጣነው ለመወያየት ነው፤ ቅዱስ ሲኖዶስ በአሁኑ ጉባኤ ይቅርታ ጠይቋል።ይህ ከሆነ መወያየት ጥሩ ነው ብለን መጥተናል።

መወያየት ክፉ አይደለም ። ሰው አሳቡን ለመግለጽም ሆነ ለመስማማትና ላለመስማማት መገናኘትና መወያየት ክፉ አልነበረም ብለዋል።

መቼም ብፁዓን አባቶች በምን ምክንያት እንደቀሩ እኛ የምናውቀው ነገር የለም ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩ በጤና ነው ወይስ አውቀው ነው ሳያውቁ ነው አምነውበት ነው ሳያምኑበት ነው የቀሩት የሚለውን እኛ የምናውቀው ነገር የለም ብለዋል።አያይዘውም ቅዲስነታቸው፤ መወያየት ጥሩ ነበር። በመወያየት አሳብን መግለጽ ይቻላል። የደረሰውን ችግር መግለጹና ማስረዳቱ አንድ ቁም ነገር ነበር። ይሁንም አይሁንም ለማለት ውይይት ጥሩ ነበር ።የሆነው ሆኖ አልተገኙም በማለት በክልሉ የሚገኙ አባቶች በውይይቱ አለመገኘታቸውን ገልጸዋል ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ቅዱስነታቸው በመቐለ ሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና ወደ ሚገኘው ቅዱስ ሚካኤል ደብር ለጸሎት ቢያመሩም፤ የቤተ ክርስቲያኑ በር ተዘግቶባቸው ቅዱስነታቸውና የመሩት የሰላም ልዑክ በር ላይ ጸሎት ለማድረስ ተገድዷል። ድርጊቱም የቅዱስነታቸውን ድምፀ ግፉዓን መሆናቸውን ከግምት ውስጥ ከአለማሰገባቱም በላይ አሳዛኝ የታሪክ ጠባሳ ሆኖ አልፏል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው ቤተ ክርስቲያን ዘግይታም ቢሆን ተጎጂዎችን ለመጎብኘትና ከብፁዓን አባቶች ጋር ለመወያየት ልዑካን መላኳ ተገቢ መሆኑን ገልጸው፤ጉዳዩ በውይይት መፈታት እንዳለበት እናምናለን ብለዋል። አያያይዘውም ይሄ ነገር አንድ እምነት በሚከተሉ ወንድማማቾች ዘንድ አንድ ማኅበር ውስጥ ባሉ ዘንድ የሚፈጠር ልዩነት በምክክር ነው መፈታት ያለበት ግን እንደ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አንገባም።

በሃይማኖት መካከል ጣልቃ አንገባም ማለት በእንደዚህ ዓይነት ምክንያቶች የሚፈጠሩ ልዩነቶች የሚፈጥሯቸው ጣጣዎች አይመለከቱንም ማለት ግን አይደለም ብለዋል።
የልዑካን ቡድኑ በትግራይ የሚገኙ ተፈናቃዮችን የጎበኙ ሲሆን ፤በነገው ዕለትም በጉዞው ዙሪያ መግለጫ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።