“ምዕመናን ገንዘባቸውን የሚሰጡት ለሃይማኖት ማስፋፊያ እንጂ ለዘረፋ አይደለም።”
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ

መስከረም ፳፫ ቀን፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም.
“””””””””””””””””””””””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
=============

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚስተዋለውን የሙስናና ብልሹ
አሰራር በዝርዝር በማጥናት የመፍትሔ ሐሳብ እንዲያቀርብ በጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት የተቋቋመው አጥኚ ኮሚቴ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖትና ከብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባህር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጋር ከተቋቋመ ጀምሮ እስካሁን የሠራቸውን ሥራዎች ሪፓርት በማቅረብ በቀጣይ በሚያከናውናቸው ተግባራት ዙሪያ በመወያየት የሥራ መመሪያ ተቀብሏል።

ኮሚቴው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚስተዋለው የመልካም አስተዳደር ችግር ከውስጥ አልፎ በአደባባይ መነጋገርያ በመሆኑ በጥናት ላይ በተመሠረተ አግባብ ተቋማዊ ለውጥ ማምጣት የሚያስችልና የቤተ ክርስቲያናችንን ክብር በሚመጥን መልኩ እንዲደራጅ የሚያደርግ የመፍትሔ ሐሳብ ለማቅረብ የሚያስችለውን ዕቅድ በማውጣት ወደ ተግባር መግባቱን የኮሚቴው ሰብሳቢ መ/ሰ ቆሞስ አባ ቃለጽድቅ ሙሉጌታ (ዶር)
እና ዲ/ን ስንታየሁ ምስጋናው ባቀረቡት ሪፖርት ገልጸዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርኩ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሰጡት አባታዊ የሥራ መመሪያ “ምዕመናን ገንዘባቸውን የሚሰጡት ለሃይማኖት ማስፋፊያ እንጂ ለዘረፋ አይደለም። ያሉ ሲሆን ስለሆነም ሕግና ሥርዓትን አክብራችሁ፣ በእውነተኝነት ለቤተክርስቲያን፣ለእግዚአብሔርና ለራሳችሁ ብላችሁ ሳታፍሩና ሳትፈሩ ሥራችሁን ሥሩ። ሥራው ታማኝነት”ጥብዓት” ያስፈልጋል ብለዋል።

ከብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ጋር ሆናችሁ በጋራ ሥሩ ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩ ጠንከር ያለ መድኅኒት ሊሆን የሚችል ጥናት ከመፍትሔ ሐሳብ ጭምር እንደምታቀርቡ እምነቴ የጸና ነው ያሉ ሲሆን አያይዘውም የተላካችሁበት ሥራ ያለ ውጤት የሚቀር መሆን የለበትም። ቤተክርስቲያን የተዋረደችበት ጊዜ ማብቃት አለበት ያሉት ቅዱስነታቸው ቤተክርስቲያናችን ራሷን አንጽታ ለሌሎች መልካም አብነት መሆን አለባት ካሉ በኋላ ዓለማዊያን የሚሰሩት ሥህተት እንዳይኖር በተግባር የምታስተምር ተቋም እንጂ በሙስና የምትታማ መሆን የለበትም ብለዋል።

ልጆቼ እውነቱን ለማውጣት ታጥቃችሁ ሥሩ በሙስና ህመም ለምትሰቃየው ቤተክርስቲያን መድኃኒት ፈልጉላት በማለት አባታዊ መልዕክታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው አንመረመርም ማለት ራሱን ችሎ ወንጀል ነው ካሉ በኋላ ይህ ሥራ ለእናንተም ታሪክ ነው። እውነትን መሰረት አድርጋችሁ በመሥራት ታሪክ አስመዝግቡ ብለዋል።

በመልዕክታቸው ማጠቃለያ ላይም ወደ እዚህ ተቋም የሚገቡ ሁሉ ይህን ያህል ጊዜ ቆይተን ይህን ያህል ይዘን እንውጣ የሚሉ እንጂ ለቤተክርስቲያን የሚቆረቆሩና የሚያስቡ እንዳልሆኑ ይታወቃል ካሉ በኋላ የተሰጣችሁን ኋላፊነት በትጋት ፈጽሙ ብለዋል።በመጨረሻም ሥራችሁ ሁሉ የተሳካና ውጤታማ እንዲሆን እንጸልያለን እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን በማለት አባታዊ መልዕክታቸውን አጠናቀዋል።