ጥር 4 ቀን 2016 ዓ.ም
“”””” “”””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
+++++++++++++
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ለሚያስገነባው ባለ ሰባት ወለል ሕንጻ የመሠረት ደንጊያ አስቀመጡ። በብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት እና የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሚመራው ፣የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የካህናት ማሰልጠኛ ሆኖ ከዘመናዊ ትምህርት ቤት እስከመንፈሳዊ ኮሌጅና ኃላም ከፍተኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ነገረ መለኮት ወይም ቲዎሎጂ ትምህርት ማስተማሪያ ፣የጥናትና ምርምር ማዕከል ሆኖ ለ60 ዓመታት ያህል መንፈሳዊ አገልግሎት መስጠቱ ይታወቃል።

ተቋሙ በእነዚህም ዘመናት ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን በርካታ ሊቃውንትን አፍርቷል። አብዛኞቹ ምሁራን በመንፈሳዊዉ ዓለም ከዲቁና እስከ ጵጵስና ፣በማኅበራዊዉ ዘርፍ ደግሞ ከመምህርነት እስከ አምባሳደርነት፣አልፎም እስከ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ በመድረስ ከዚሁ ከፍተኛ መንፈሳዊ ተቋም ባገኙት ዕውቀት እና ጥበብ በተለያዩ የሥራ መስኮች ሀገራቸውንና ቤተ ክርስቲያናቸውን በከፍተኛ ሐላፊነት ሲያገለግሉ መቆየታቸው አይዘነጋም።አንጋፋውና የዕድሜ ባለጸጋው የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ጊዜ ከትምህርትና አስተዳደር ዘርፍ ጎን ለጎን በራስ አገዝ ልማት ከፍተኛ የለውጥ ሥራዎች ግሥጋሴ ላይ የሚገኝ ሲሆን ከዚህ ቀደም ከፓርላማ እስከወክማ ከተገነባው ሽንጠ ረጅምና ሰማይ ጠቀስ ሕንጻ በተጨማሪ ከሦስት ሺህ በላይ ባለው የካሬ ሜትር ስፋት ላይ ባለሰባት ወለል ሁለገብ ሕንጻ ለመገንባት ጥር 4 ቀን 2016 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባህር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ክቡር ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ፣የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ሐላፊዎች፣የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የሥራ ሐላፊዎች፣የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብና ደቀመዛሙርት በተገኙበት የመሠረት ደንጊያ የማኖር መርሐ ግብር ተካሂዷል።መርሐ ግብሩ በጸሎተ ወንጌል የተከፈተ ሲሆን በማያያዝም ዕብነ መሠረቱ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩና በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ተቀምጧል።የ

ሕንጻውን የዲዛይን ይዘት በተመለከተ በባለሙያ ማብራሪያ ተሰጥቷል። በተያያዘም በዩኒቨርሲቲው ግቢ ዕድሳት ተደርጎለት አገልግሎት የጀመረው መንበረ ጵጵስና በቅዱስ ፓትርያርኩና በብፁዓን አባቶች ተጎብኝቷል።ዛሬ ለመንበረ ጵጵስና የበቃው ቤት በንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መጻሕፍትን የምትተረጉምበት፣ በኮፕቲክ ሲኖዶስ ተሹመው ወደሀገራችን የመጡት ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት (የመጀመሪያዎቹ አምስቱ ሊቃነ ጳጳሳት )ማረፊያ የነበረ ሲሆን አሁን እስከተደረሰበት የመንበረ ጵጵስና ደረጃ ድረስ ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብና ደቀ መዛሙርት የጸሎት ማዕከል ሆኖ ሲያገለግል መቆዩቱን የዩኒቨርሲቲው የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።