መስከረም 29 ቀን 2016ዓ.ም.
+ + +

የጋምቤላ ፣ የቄለም ወለጋ፣ የአሶሳ፣ የምዕራብ ወለጋ ፣ የሆሮ ጉድሩ ፣ የምስራቅ ወለጋ እና የደቡብ ሱዳን አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣ የጋምቤላ ክልል እና የቤኒ ሻንጉል ክልል የሰላምና የልማት አንባሳደር ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል ከሐምሌ 2016ዓ.ም. ጀምሮ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉዞ በስድስቱ አህጉረ ስብከት ታላላቅ መንፈሳዊ ጉዞዎችን አድርገዋል።

በጉዟቸው የተዘጉ አቢያተክርቲያናትን በማስከፈት ፣ ከህግ ውጪ የነበሩ ቡድኖችን በማስተማርና ወደህግ በማስገባት ፣ ፐርሰንት የማይከፍሉ አቢያተክርስቲያናትን እንዲከፍሉ በማድረግ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን በመሥራት ቆይታ አድርገዋል። በተለይም በአራቱ ወለጋዎች በህገ ወጥ ሹመት ምክንያት ተደረጅተው የነበሩ ቡድኖችን አንዲት ሃይማኖት ፣ አንድ ሲኖዶስና አንድ ፓትርያርክ ብለው እንዲያምኑ በማድረግና በምዕራብ ወለጋ በህገ ወጥ ተሿሚዎች ክህተነት ተሰጥቷቸው የነበሩ ከ100 በላይ የሚቆጠሩ ካህናትንና ዲያቆናትን ቀኖና በመስጠት በመጨረሻም በብፁዕነታቸው ክህነት ተሰጥቷቸው ወደ አገልግሎት እንደመለሱ ተደርጓል።

በምዕራብ ወለጋ የሚገኘው መንበረ ጵጵስና በህገ ወጥ ተሿሚዎች ቁልፉ ተሰብሮ፣ መስኮትና በሮቹ ተገንጥለው የነበረ ቢሆንም ብፁዕነታቸው ወደ ሀገረ ስብከቱ ከገቡ በኋላ እድሳት ተደርጎለት እና ተባርኮ ደግም አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። ብፁዕነታቸው ወደ ሀገረ ስብከቱ ሲገቡ ከጊንቢ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገቸው የዩብዶ ወረዳ ካህናትና ምዕመናን ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ብፁዕ አባታችንም “ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር” በሚል ርዕስ አባታዊ ምክርና ቃለ ምዕዳን ሰጥተዋል።

በመቀጠልም የምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት ሠራተኞችን በመሰብሰብ ከዚህ በኋላ በህገ ቤተክርስቲያን መሠረት ሥራቸውን እንዲቀጥሉ መመሪያ በመስጠትና እስከ አሁን ያልተከፈላቸውን ደመወዝ በመከፈል በአዲስ መልክ ሥራ እንዲጀምሩ አድርገዋል። የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞችም የብፁዕነታቸውን አባታዊ መመሪያ በመቀበል ዳግም ወደ ሀገረ ስብከታችን ስለመጡልን እግዚአብሔርን እያመሰገንን ሥራችንን ጀምረናል ብለዋል።

በመጨረሻም የኦሮሚያ ቤተክህነት እናደረጃለን እያሉ በሀገረ ስብከቱ የሚነቀሳቀሱትን ልዩ ልዩ ቡድኖች ወደ ህግ እንዲቀርቡ በተረገላቸው ጥሪ መሠረት አብዛኞቹ ወደ ቤተክርስቲያን አንድነት የቀረቡ ሲሆን የማሰላሰያ ጊዜ የሚፈልጉ ጥቂት ግለሰቦችንም ወደ በረቱ እንዲመለሱ ጥሪ ቀርቦላቸዋል። እንደ ሀገረ ስብከቱ ሕዝብ ግንኙነት ገለጻ ከሆነ ብፁዕነታቸው ለጥቅም ሲኖዶስ ከመመለሳቸው በፊት ሁሉም ተጠቃለው እንደሚገቡ የሚታመን ነው ተብሏል።

ዘገባውን ያደረሰን የሀገረ ስብከቱ ሕዝብ ግንኙነት ነው።