መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ዓ.ም
“””””””””””””””””””””””””””””

የአቡዳቢ መንግሥት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሰጠው ቦታ ላይ የአቡዳቢ ደብረ ሰላምን መድኃኔዓለም ካቴድራል መቃኞ ቤተ ክርስቲያን መገንባቱ ይታወሳል።

እንደ ሊባኖስ፣የተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስ እና የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ዘገባ የመቃኞ ቤተ ክርስቲያኑ ቅዳሴ ቤት ተከብሮ አገልግሎት ለመጀመር በአቡዳቢ ሃይማኖታዊ እና ማኅበረሰባዊ ጉዳዮችን ከሚያስተዳድረው የኅብረሰብ እድገት ክፍል ( Department of Community Development- DCD) ፈቃድ ማግኘት የግድ ያስፈልጋል።

በመሆኑም ትናንት መጋቢት 27/2015 ዓ.ም የ DCD ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር ሙግሔር አል ካሀሊ የአቡዳቢ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ካቴድራልን የፈቃድ ሰነድ ለብፁዕ አቡነ ድሜጥሮስ የሊባኖስ፣ የተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስ እና የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አስረክበዋል።

ክቡር ዶ/ር ሙግሔር አል ካሀሊ ብፁዕነታቸውን በማግኘታቸው ታላቅ ደስታ እንደተሰማቸው ከገለጡ በኋላ ኢትዮጵያውያን ለኢሜሬትስ እድገት ብዙ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ብለዋል። አያይዘውም በሚያስፈልጋችሁ ሁሉ ከጎናችሁ ነን ሲሉ ቃል ገብተዋል።

ብፁዕ አቡነ ዲሜጥሮስም የኢሜሬትስ መንግሥት ላደረጉት በጎነት ምስጋና ካቀረቡ በኋላ ኢሜሬትስ የነጻነት ምድር፣ የሰላም ሀገር፣ የእስልምና አማናዊ መልክ፣ የስደተኞች ማረፊያ፣ እድገት ከባህል፣ ሥልጣኔ ከሞራል ጋር የተባበሩባት ናት ብለዋል። ወደ ፊት በሚኖረው ፍላጎትም ዙሪያ እገዛቸውን ጠይቀዋል።