በራያና አካባቢው የሚገኙ ስድስት ወረዳዎችን እንዲያስተባብር የተቋቋመው ጽሕፈት ቤት በ፵፪ኛው ዓለምአቀፍ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን አቀረበ።

ጥቅምት ፯ ቀን ፳፻ ፲ ወ፮ ዓ.ም
“”””””””””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
******
በሐምሌ ወር ፳፻ ፲ወ ፭ ዓ.ም አስቸኳይ ጉባኤውን ያካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በራያና አካባቢው ከሚገኙ ስድስት ወረዳዎች የቀረበለትን ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት ይቋቋምልንና የሀገረ ስብከታችን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ እንዲመሩን ይፈቀድልን በማለት ያቀረበውን ጥያቄ በመቀበል ችግሩ እስከሚፈታ ድረስ በአካባቢው የሚገኙ ምዕመናን አገልግሎት ማግኘት ይችሉ ዘንድ ጽሕፈት ቤቱ እንዲቋቋም ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ ተቋቁሞ ፣ቢሮ ተከራይቶና ኃላፊዎች ተመድበውለት ሥራውን በማከናወን ላይ መሆኑ ይታወቃል።

በዚህም መሰረት ጽሕፈት ቤቱ ሥራውን በመጀመር በርካታ ተግባራትን በአጭር ጊዜያት ያከናወነ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ለ፵፪ ኛው አጠቃላይ ዓለም አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ሪፖርቱን ሲያቀርብ የፐርሰንት ገቢውን ደግሞ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በሊቀ ጳጳሱ በብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ አማካኝነት ገቢ አድርጓል።

ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ በሪፖርቱ ላይ እንደገለጸው በጦርነቱ ያጋጠመው ችግር ቁስሉ ሳይሽር ራሱን መንበረ ሰላማ የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በማለት የሚጠራው ቡድን ቀኖናን ጥሶ፣ሕግን አፍርሶ፣በሚወስነው ውሳኔና በሚሰጠው መግለጫ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርካችን ከምትመራው ቤተክርስቲያናዊ መዋቅራችን ጋር እንዳንገናኝ፣ እንድንለያይና ስሟን እንዳንጠራ፣ምንም ዓይነት አሳማኝ ታሪካዊ ምክንያት በሌለው ሁኔታ ገደብ ተጥሎብን ስንጨነቅ ቆይተናል ብሏል።

ይኸው ቡድን ይህን ሁሉ ማድረጉ ሳያንሰው ባለፉት ፲፰ ዓመታት በችግራችን ፣በሐዘናችን፣በደስታችንና በመከራችን በጽናት ከእኛ ጋር በመቆም ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን በማክበርና በማስከበር በአንድነትና በፍቅር ሲባርኩን፣ሲያጽናኑን፣ሲያስተምሩንና ሲመሩን የነበሩት አባታችን ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስን በተራዘመ ውሸት በሚዲያ በማብጠልጠልና መልካም ስማቸውን በማጠልሸት ሕዝባቸውን እንዳይባርኩና እንዳያጽናኑ ተደርጓል ብሏል።

በዚህ እኩይ ተግባር ሕዝቡ ሰብሳቢና አጽናኝ አባት አጥቶ ተበትኖ እንዲቀር የተደረገውና እየተደረገ ያለውም የስም ማጥፋት ዘመቻ ለእርስ በእርስ ግንኙነት የማይጠቅምና ሀብለ ፍቅርን የሚበጥስ፣ታሪክን የሚያጎድፍ አሳፋሪ ተግባር ነው ብሎታል።

የማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤታችን እንዲቋቋምና አሁን እያከናወነ የሚገኘውን ውጤታማ ተግባር እንዲፈጽም አስፈላጊውን ትብብር ሁሉ ላደረጉልን ለብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ለብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ዶ/ር የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒውዮርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ለብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ምስጋናችንን በዚህ ታላቅ ጉባኤ ፊት ለማቅረብ እንወዳለን ብሏል።

ለወደፊቱ በብፁዕ አባታችን አቡነ ዲዮስቆሮስ መሪነት በርካታ ሥራዎችን በማከናወን ውጤታማ ሥራ ሰርተን የሚጠበቅብንን ውጤት በማስመዝገብ የተሻለ የፐርሰንት ገቢ ይዘን እንደምንገናኝ ጽኑዕ እምነት አለን ያለው የጽሕፈት ቤቱ ሪፖርት ለአሁኑ በሁለት ወራት የሥራ እንቅስቃሴያችን ከሰበሰብነው ገቢ የጠቅላይ ቤተክህነት ድርሻ የሆነውን ብር ፪፻ ሺህ ብር ለበረከት ያቀረብን መሆናችንን እንገልጻለን በማለት ገቢ የተደረገበትን የባንክ ስሊፕ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ አማካኝነት አስረክቧል።