በሲነርጂ ሀበሻ ፊልምና ኮሚኒኬሽን በመዘጋጀት ላይ የሚገኘው የሰማዕቱ ሊቀ ጳጳስ የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ፊልም ጽሑፍ በሊቃውንት ጉባኤ እንዲመረመር ታዘዘ።

ኅዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም
“””””””””””””””””””””””””
አዲስ አበባ -ኢትዮጵያ
==============

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ሲነርጂ ፊልምና ኮሚኒኬሽን በኢትዮጵያዊው ሰማዕት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሊቀ ጳጳስ የስማዕትነት ተጋድሎ ዙሪያ የሚያጠነጥን ፊልም ለመስራት የሚያደርገው እንቅስቃሴታሪክን የሚያጎድፍ ሆኖ ስለተገኘ ሊቆም እንደሚገባ በመግለጽ ኅዳር 25 ቀን 2016ዓ.ም በቁጥር 1673/2789/2016 በተጻፈ ደብዳቤ መግለጹ ይታወሳል።

ይህንን ተከትሎ የፊልሙ ጸሐፊ እና ዳይሬክተር ሞገስ ታፈሰ ዶ/ር እየተዘጋጀ የሚገኘውን ፊልም ቤተክርስቲያናችን በሊቃውንቶቿ አማካኝነት መርምራ፣ የሚታረም ካለ አርማና የሚቃናውን አቅንታ በምትሰጠን አስተያየትና ማስተካከያ መሠረት ፊልሙን የምንሠራ መሆኑ ታውቆ አስፈላጊው ትብብር ሁሉ ይደረግልን። በማለት በጽሑፍና በአካል ጠቅላይ ቤተ ክህነት በመገኘት በፊልሙ ዝግጅት ዙሪያ ማብራሪያ በመስጠት ለተፈጠረው የመረጃ ክፍተት ይቅርታ ጠይቀዋል።

ብፁዕ አቡነ አብርሃም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስም ዶ/ርሞገስ ታፈሰ ያቀረቡትን ይቅርታ በመቀበል በአካልና በጽሑፍ በፊልሙ ጽሑፍ ዝግጅት ዙሪያ መረጃ ከመስጠት ባለፈ በቤተ ክርስቲያናችን በኩል የፊልሙ ጽሑፍ እንዲመረመርላቸውና እርማት በሚያስፈልገው ጉዳይ ዙሪያ እርማት እንዲደረግበት መጠየቃቸው የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህን ተከትሎም የፊልም ጽሑፉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ጉባኤ በሚገባ ተመርምሮና መታረም ያለበት ሁሉ ታርሞ እንዲቀርብ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ መመሪያ የተሰጠ ሲሆን የፊልም ጽሑፉም በሊቃውንት ጉባኤ እየተመረመረ መሆኑ ታውቋል። ሊቃውንት ጉባኤ የፊልሙን ጽሑፍ መመርመሮ ሲያጠናቅቅም ውጤቱን የምንገልጽ ይሆናል።