ሐምሌ 19/2016 ዓ/ም
“”””””””””””””””””””””””””””””””
በዕለቱ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የምዕራብ ትግራይ ማይጨው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክቡቡር አቶ መኩሪያ መርሻዬና ሌሎችም የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎ፣ የሀዋሳ ከተማና ዙሪያ ወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች የተገኙ ሲሆን በዐውደ ምሕረትም በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና በሰ/ት/ት ቤት መዘምራን ያሬዳዊ ወረብ ከቀረበ በኋላ የሀዋሳ ወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ላዕከ ወንጌል ደግፌ ባንቡራ መልእክት አስተላልፈው ክቡር ከንቲባውን ጋብዘዋል።
ክቡር ከንቲባውም የቅዱስ ገብርኤል አምላክ ረድቶን ከታኅሣሥ ዛሬ ደረሰን እንድናከብር የረዳን እግዚአብሔር ስለሆነ እናመሰግናለን።

የዛሬውም በዓል እናትና ልጅ ከሃይማኖታቸው ውጭ የመጣባቸውን እንቢ በማለታቸው ወደ እሳት ቢጣሉም ታላቁ መልአክ እንደ ታደጋቸው የሚነገርበት ዕለት እንደ ሆነ አባቶቻችን ያስተምሩናል።
ስለዚህ ይህ በዓል የኦርቶዶክሳውያን ብቻ ሳይሆን የከተማችን በዓል ነው በአጠቃላይ ይህን በዓል ስናከብር ከሚያመልኩት ውጭ እንዲያመልኩ ሲጠየቁ እንቢ እንዳሉት እኛንም ከአብሮነታችን ከሰላማችን ውጭ መለያየትን ጥላቻን የሚያመጡትን እናትና ልጅ እንዳረጉት እንድታደርጉ አደራ ማለት እፈልጋለሁ በማለት መልእክት አስተላልፈዋል።

በመቀጠል የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ፀሐይ ቆሞስ አባ ኪደነ ማርያም አንዱዓለም ለበዓሉ መሳካት አስተዋጽኦ ያደረጉትን ከሀገረ ስብከቱ ጀምሮ የመንግሥት አካላትንና ምእመናን ካመሰገኑ በኋላ በግቢ ውስጥ እየተሠራ ያለውን የልማት እንቅስቃሴ ገለጸው የሀገረ ስብከቱን ሊቀ ጳጳስ ጋብዘዋል።

ብፁዕ አቡነ ዮሴፍም ቅዱስ ቂርቆስና ቅድስት ኢየሉጣ በእምነታቸው በመጽናታቸው እናከብራቸዋለን ስለዚህ እኛም መጽናት አለብን።ሌላው ቤተ ክርስቲያን ኀዘን ላይ ናት ጎፋ አካባቢ በተፈጠረው ውስጣችን ተሠብሯል።

በጸሎት እናስባቸዋለን ኮሚቴ አዋቅረን ገንዘብ አሰባስበን በአካል ሄደን እናጽናናለን ኅዘናችን ግን ጥልቅ ነው በማለት አባታዊ መልእክት አስተላላፊው የዕለቱን ትምህርት እንዲያስተምሩ መድረኩን ለብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ሰጥተዋል።
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስም “ወኩን መሀይመ እስከ ለሞት ወእሁበከ አክሊለ ሕይወት” እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወት አክሊል እሰጥሀለሁ ራዕ 2፥10 በሚል ርእስ ተነስተው የቅድስት ኢየሉጣንና የቅዱስ ቂርቆስን የእምነት ጽናት አንስተው ሰፊ ትምህርት አስተምረዋል።

በመጨረሻም በጎፋ አካባቢ በአዳጋ የሞቱትን እረፍተ ነፍስ እንዲሰጣቸው የተጎጂ ቤተሰቦችን እግዚአብሔር እንዲያጽናናቸው
አባታዊ መልእክትና ቡራኬ ሰጥተው በብፁዕነታቸው ጸሎት የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል።©የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሕዝብ ግንኙነት