ሐምሌ ፫ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ዓ.ም
*****
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
******

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለክልል ትግራይ የሰብዐዊ ድጋፍ እንዲደረግና ቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በትግራይ ክልል ከሚገኙ አባቶች ጋር ውይይት እንዲደረጉ ውሳኔ አስተላልፏል።

ይህ በእንዲህ እያለ ቀደም ሲል የተቋቋመው ኮሚቴው ወደ ክልሉ ከመጓዙ አስቀድሞ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የሚመራ ልዑካን ቡድን ወደ መቐለ እንዲጓዝና የሰብዐዊ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ በክልሉ ከሚገኙ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ውይይት አድርጎ እንዲመለስ በቋሚ ሲኖዶስ መወሰኑና ይኸው በመቐለ ሊካሔድ የታሰቀው መርሐ ግብርም አስቀድሞ ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲደርስ ተደርጓል።

በዚህም መሰረት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የሚመራ ፲፰ አባላት ያሉት የልዑካን ቡድን ዛሬ ሐምሌ ፫ቀን ፳፻ ፲ወ፭ዓ.ም ማለዳ ወደ ክልል ትግራይ መቐለ ከተማ አምርቷል።

ልዑካን ቡድኑ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በመገኘት የሰብዐዊ ድጋፉን የሚያበረክት ሲሆን በክልሉ ጊዜያዊ መንግስት በኩል በሚመቻቸው መሠረት ተፈናቃይ ወገኖችን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በመርሐ ግብሩ መሰረትም ቅዱስ ፓትርያርኩና የልዑካን ቡድኑ አባላት በትግራይ ከሚገኙ ብፁዓን አባቶች ጋር ውይይት ያደርጋሉ።ቅዱስ ሲኖዶስ በቅርቡ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት የትግራይን ሕዝብ ይቅርታ መጠየቁ ይታወሳል።