በትግራይ ክልል ከሚገኙ አባቶች ጋር ውይይት ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተጠናቀቀ።

ሰኔ ፫ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም
“”””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
******

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በግንቦት ወር ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም ባካሔደው የርክበ ካህናት ጉባኤ በትግራይ ክልል ከሚገኙ አባቶች ጋር የሚደረገው ውይይት ቀደም ሲል በቋሚ ሲኖዶስ በተሰየመው የልዑካን ቡድን አማካኝነት በአስቸኳይ እንዲቀጥል መወሰኑ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ ኮሚቴው ውይይቱን በተሳካ ሁኔታ ለማካሔድ የሚያስችለውን በእቅድ ላይ የተመሰረተ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ሲያከናውን የቆየ ሲሆን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ውይይቱ በተሳካ ሆኔታ መካሔድ የሚችልበትን ሁኔታ እንዲያመቻች በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በተጻፈ ደብዳቤ ጥያቄውን አቅርቧል።የልዑካን ቡድኑ አባላትም ከቅዱስ ፓትርያርኩ የተጻፈውን ደብዳቤ በአካል በመገኘት ለክልሉ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት በማቅረብ ከሚመለከታቸው የክልሉ የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር የክልሉ ጊዚያዊ መንግስት ለውይይቱ መሳካት በሚያደርገው ድጋፍ ዙሪያ ውይይት በማድረግ ተመልሷል።

ስለሆነም ለክልሉ መንግስት በቀረበው ጥያቄ መሰረት ሁለቱም አካላት በሚያመቻቹት ጊዜና ቦታ ውይይቱ የሚካሔድ ይሆናል። በዚህም መሰረት የጠቅላይ ቤተክህነት ልዑካን ቡድን ውይይቱን ውጤታማ ለማድረግ ይቻል ዘንድ እስከ አሁን ያከናወናቸውን ተግባራትና ወደፊት ውይይቱን ስኬታማ በሆነ መንገድ ማካሔድ በሚችልበት ሁኔታ ዙሪያ ሰኞ ሰኔ ፭ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ይፋዊ መግለጫ ይሰጣል።መግለጫውን ተከትሎም ጉዳዩ በቀኖና ቤተክርስቲያን መሰረት የመጨረሻ እልባት እንዲያገኝ በፍጥነት ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በመግባት በሒደቱ የሚመዘገቡ ለውጦችን ሁሉ በመገናኛ ብዙሃን የሚያሳውቅ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
ሰኔ ፫ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ