በአዲሱ ዓመት ቅድስት ቤተክርስቲያን ትኩረት ሰጥታ መሥራት ያለባትን ጉዳዮች ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል ሊቀጳጳስ አስታወቁ።

በአዲሱ ዓመት ቅድስት ቤተክርስቲያን ትኩረት ሰጥታ መሥራት ያለባትን ጉዳዮች ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል ሊቀጳጳስ አስታወቁ።
“””””””””””””
1. ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ በመልዕክቱ “ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም ይህን ወይም ያን እናደርጋለን ማለት ይገባችኋል።” (ያዕ 4÷15) እንዳለው
ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነትን ጀምሮ በመላው ዓለም ባሉት አደረጃጀቶች ዘንድ ዘላቂነት እና ወጥነት ባለው መልኩ ዘመኑን የዋጀ ተቋማዊ አሠራር አገልግሎቱን ለማሳለጥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በረጅም እና በአጭር ጊዜያት የሚተገበሩ የአገልግሎት አቅጣጫዎችን፣ አጠቃላይ የመሪ ዕቅድ ስልቶችን እና መርሐ ግብሮችን በየደረጃው ያለው የቤተክርስቲያን መዋቅር መፈጸም ይጠበቅበታል፤

2. የቅድስት ቤተክርስቲያን አንድነት እየተፈታተነ ያለ ክፍፍል በተለይም በኦሮሚያ እና በትግራይ የታየውን ወደ አንድነት ማምጣትና በዕርቅ፤ በሰላም እና በስምምነት መፈጸም ይገባናል፤ ይህንንም ለመፈጸም የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግስታት ከቅድስት ቤተክርስቲያን ጎን ሆነው ሕግ የማስከበር ሥራ እንዲሠሩ አበክረን መሥራት ያስፈልገናል፤

3. በመንፈሳዊ ማኅበራት የሚሠሩ ሥራዎች ፤ በሰ/ት/ቤት ለአዳጊዎች እና ለወጣቶች የሚሰጧቸው ሁለገብ አገልግሎቶች በዓለማችን ላይ በየጊዜው የሚከሰተቱን መልካም ዕድሎች እና ፈተናዎች እንዲሁም በየአህጉረ ስብከቱ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከክርስቲያናዊ ዕሴቶች ጋር ባገናዘበ መልኩ እንዲተገበሩ በመንፈሳዊ ጥበብ የተቃኙ ቀልጣፋ የአፈጻጸም ስልቶችን በመከተል መሥራት አለብን፤

4. ሕገ-ወጥ አጥማቂያንን እንዲሁም በየቦታው ያለቅድስት ቤተክርስቲያን ፈቃድና ዕውቅና በመንቀሳቀስ ዶግማዋን ቀኖናዋን እና ሥርዓቷን የሚጥሱ ግጭት የሚቀሰቅሱትን የተደራጁ ኃይሎችን እና ግለሰቦችን ሥርዓት ማስያዝ፤ በተጨማሪም በዓመቱ በርካታ ፓስተሮች እየተጠመቁ ከተከታዮቻቸው ጋር ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን ስለተመለሱ ማጽናትና መንከባከብ አለብን፤

5. የመሪ ዕቅዱን አፈጻጸም ባለው ሂደት ውስጥም በመላው ዓለም ከመንበረ ፓትርያርክ ጀምሮ እስከ አጥቢያ ሰ/ጉ/ቤት ድረስ በተዘረጋው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መዋቅራዊ አደረጃጀት ውስጥ በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር ተሰባስበው ለአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮ እና ራእይ መሳካት ሁለገብ እና ጉልህ ሚና የሚጫወቱ አገልጋዮችን ማበረታታትና ማሳደግ በአዲሱ ዓመት የቅድስት ቤተክርስቲያን የትኩረት አቅጣጫ መሆን ይገባል ብዬ አምናለሁ ሲሉ ብፁዕነታቸው ተናግረዋል።

መስከረም 06 ቀን 2017 ዓ/ም
አሶሳ፤