* በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
* ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ ባሕር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
* ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
እኛ በማኅበራዊ ሚዲያ በተለያየ መንገድ አሳባችንን በመግለጽና አዎንታዊ መረጃዎችን በመስጠት የእናታችን የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ አገልግሎት ለማገዝ የምንሠራ የቤተክርስቲያናችን ልጆች ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ያቀረበችልንን ጥሪ በመቀበልና ሚያዝያ 5 እና 6 ቀን 2016 ዓ/ም ‹‹ኦርቶዶክሳውያን ብዙኀን መገናኛ ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን›› በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀችልንን የሥልጠና፣ የምክክርና የውይይት መርሐ-ግብር በመሳተፋችን እጅግ ታላቅ ደስታ ተሰምቶናል፡፡
በሥልጠናው ላይ የጥናት ጽሑፎችን በማቅረብ ግንዛቤን የሰጡን የቤተ ክርስቲናችን ምሁራንም ያቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ ማኅበራዊ ሚዲያን በተመለከተ በቂ ግንዛቤን የሰጠን ከመሆኑም በላይ ቤተ ክርስቲያናችን እንዲህ ያሉ ምሁራን ያሏት መሆኑን አስገንዝቦናል፡፡
ያለንበት ወቅት ቤተ ክርስቲያናችን በተለያዩ ውስጣዊም ሆነ ውጪያዊ ፈተናዎች የተወጠረችበት ከመሆኑም ባሻገር እነዚህ ፈተናዎች ግዘፍ ከሚነሱባቸው መስኮች አንዱ የማኅበራዊ ሚዲያው ዘርፍ መሆኑን ተረድተናል፡፡
እናት ቤተክርስቲያናችን በዚህ መንገድ እየተፈተነች መሆኑን የተገነዘበው የቤተክርስቲያናችን ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ‹‹የሀገሩን ሰርዶ በሀገሩ በሬ›› እንደሚባለው በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል የሚከሰቱ ፈተናዎችን መከላከል የሚቻለው በዘርፉ ባሉ የቤተክርስቲያን ልጆች መሆኑን ተገንዝቦ ከቤተክርስቲያናችን ጎን ቆመን ፈተናዎችን በጋራ መከላከል እንድንችል የተደረገልንን የልጅነት ጥሪ በደስታ ተቀብለናል፡፡
ስለሆነም ለሁለት ቀናት የተሰጠንን ሥልጠና መነሻ በማድረግ ባከናወንነው የቡድን ውይይት የሚከተሉትን የአክብሮት የልጅነት ጥያቄ የቤተክርስቲያናችን ርእሰ አበው በሆኑት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት እና በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ፊት በማቅረብ የቤተክርስቲያናችንን መንፈሳዊ፣ አስተዳደራዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ለማገዝ በልጅነት የሚቻለንን ሁሉ ለማድረግ እንደሚከተለው ቃል እንገባለን፡፡
እኛ በማኅበራዊ ሚዲያ የቤተክርስቲያንን መልካም ገጽታ ለመገንባትና ጎጂ ተግባራት የሚወገዱበትን መረጃ ለማኅበረሰብ የምናደርስ የቤተክርስቲያን ልጆች፡-
1- በተደረገው የሥልጠና፣ የውይይትና የምክክር መርሐ-ግብር ደስተኞች በመሆናችን የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር ጠብቀን ከቤተ ክርስቲያናችን የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ጋር በጋራ ለመሥራት የምንችልበት አስፈላጊው መደላድል እንዲፈጠርልን በልጅነት እንጠይቃለን፡፡
2- ቤተ ክርስቲያናችን ለማኅበረሰብም ሆነ ለምእመናን አስፈላጊውን መረጃ በወቅቱ ማድረስ የምትችልበትን አሠራር እንድታጠናክር እንጠይቃለን፡፡
3- በቤተ ክርስቲያን ስም የሚወጡ የሐሰት ዜናዎችን እየተከታተለ የሚያጋልጥ አሠራር እንዲዘረጋ እንጠይቃለን፡፡
4- የቤተ ክርስቲያን ልጆች በሚዲያ አምባሳደርነት ተካተው ቤተ ክርስቲያናችንን በማኅበራዊ ሚዲያው ዘርፍ እንዲያግዙ የሚያደርግ አሠራር እንዲዘረጋ እንጠይቃለን፡፡
5- የቤተ ክርስቲያን ልጆች እንደሆኑ በሚገልጹ የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች የሐሰት አስተምህሮ እንዲሁም በተለያዩ ክብረ በዓላት ላይ የቀጥታ ሥርጭት የሚያስተላልፉ አካላት ከቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና እና ነባር ባሕለ-ሃይማኖት ጋር የሚጋጩ ተግባራትን እየፈጸሙ በመሆናቸው ምክንያት የሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አጠባበቅ ላይ ከፍተኛ ክፍተቶች እየተፈጠሩ በመሆኑ ሚዲያን የተመለከተ ጠንካራ ሕግ እንዲወጣ እንጠይቃለን፡፡
6- በማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን ላይ ክፍተቶች እየተፈጠረ ያለው ከግንዛቤ ማነስ በመሆኑ እንዲህ ያሉ የሥልጠና፣ የውይይትና የምክክር መድረኮች ተደጋግመው ይዘጋጁልን ዘንድ እንጠይቃለን፡፡ ወደፊት በሚዘጋጁ ተመሳሳይ መርሐ-ግብሮች ላይም ከእኛ ጋር በንቃት የሚሳተፉ የቤተ ክርስቲያን ልጆችን ለእናት ቤተ ክርስቲያናችን ድምጽ ይሆኑ ዘንድ ወደ መርሐ-ግብሩ ለመጋበዝ ቃል እንገባለን፡፡
7- ከግል ዝንባሌ፣ ከወገንተኝነት፣ ከጥቅመኝነት፣ ከዘርና ከዝምድና አስተሳሰብ ነጻ በሆነ መንገድ ቤተ ክርስቲያናችንን በዘርፉ ለማገልገል ቃል እንገባለን፡፡
8- የሚዲያ የሥነ-ምግባር ሕግጋትንና ክብረ ክህነትን ባከበረ መንገድ መረጃዎቻችንን ለማስተላለፍ ቃል እንገባለን፡፡
9- የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች መሆናችንን የሚገልጹ አርአያዎችን በመያዝና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን በመረጃ ምንጭነት በመጠቀም መረጃዎቻችንን ለማስተላለፍ ቃል እንገባለን፡፡
10- የቤተ ክርስቲያናችንን አበው፣ ሊቃውንትና ንዋየ ቅድሳት በምንጠራበት ወቅት ቤተ ክርስቲያናችን የምትጠቀምባቸውን ቀኖናዊ ሥያሜዎች ብቻ በመጠቀም ለመጥራት ቃል እንገባለን፡፡
ይህንንም የገባነውን ቃል ለመጠበቅ እንድንችል የብፁዕ ወቅዱስ አባታችን እና የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት አባቶቻችን ጸሎት ትርዳን፡፡
ሚያዝያ 7 ቀን 2016 ዓ/ም
አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ