“ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን በጣስ መልኩ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን እና ሥርዓተ አምልኮ በዲጂታል ሚዲያ የሚያስተላልፉ አገልጋዮች እና ሌሎች የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ከድርጊታቸው መቆጠብ ይገባቸዋል” ብፁዕ አቡነ አብርሃም
“””””””””””””””””””””
ሚያዚያ ፮ቀን ፳፻ ፲ወ፮ዓ.ም
*******
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
=============
ኦርቶዶክሳውያን ብዙኃን መገናኛ ለኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሥልጠና በሁለተኛው ቀን ውሎ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባህር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት መልዕክት ” ሐሰተኛ ወሬ አትቀበል፤ ሐሰተኛ ምስክርም ትሆን ዘንድ ከኃጢአተኛ ጋር እጅህን አታንሣ ክፉውን ለማድረግ ብዙ ሰዎችን አትከተል፤ ፍርድንም ለማጥመም ከብዙ ሰዎች ጋር ተስማምተህ አትመስክር ” ዘጸ 23፥1-2 በሚለው የቅዱስ መጽሐፍ ቃል በመነሳት መልዕክት አስተላልፈዋል።

ብፁዕነታቸው ኦርቶዶክሳውያን ብዙኃን መገናኛ ተቋማትና ማኅበራዊ ሚዲያዎች ሐሰተኛ ወሬ ባለመቀበል እና ባለማስተላለፍ ኃላፊነታቸውን ሊውጡ እንደሚገባ ገልጸዋል።
“ኦርቶዶክሳውያን ብዙኃን መገናኛ ለኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን” በሚል ርዕስ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ያዘጋጀው ሥልጠና ውይይት እና ምክክር መርሐ ግብር የቡድን ውይይት የተጠቀሱ ችግሮች እና የተነሱ የመፍትሔ ሐሳቦችን በማዳመጥ በውይይቱ ከተጠቀሱት ውስጥ ብፁዕነታቸው ትኩረት በሚያስፈልገቸው ነጥቦች ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ቤተክርስቲያንን ሳያውቁ ተገቢው ሙያና እውቀት ሳይኖራቸው የሃይማኖት አስተምህሮ ለማስተላለፍ እና በየማኅበራዊ ሚዲያው እና ዲጂታል ሚዲያው ለመንቀሳቀስ የሚሞክሩ እንዳሉ በውይይት መነሳቱን የጠቆሙት ብፁዕነታቸው እውቀቱ ሳይኖራቸው ቤተክርስቲያንን ወክሎ ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ማስተላለፍ እንደማይገባ ገልጸዋል ::

ማኅበራዊ ሚዲያውና ዲጀታል ሚዲያው ከቤተክርስቲያን ይልቅ ለግለሰቦች እና ለቡድን ፍላጎቶች የመቆም ዝንባሌ በሰፊው ይታያል ሆኖም ቅድሚያ ለቤተክርስቲያን መስጠት ይገባል ያሉት ብፁዕነታቸው ገንዘብ መስብሰብን ዓላማ ያደረገ የዲጂታል ሚዲያ እና ማኅበራዊ ሚዲያ ሥራ በመንፈሳዊ ቅኝት ያልተቃኘ በመሆኑ እርምት የሚሻ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ መንበረ ፓትርያርክ ከዲጂታል ሚዲያዎች ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት የተጀመሩ ሥራዎች እንደሚቀጥሉ የገለጹት ብፁዕነታቸው ; በዲጂታል ሚዲያ እና ማኅበራዊ ሚዲያ የሚያገለግሉ እና የሚገለግሉ የቤተክርስቲያን ልጆች ለቤተክርስቲያን ከማይጠቅሙ አጀንዳዎች ራሳቸውን እንዲያርቁ መክረዋል።

በዲጂታል ሚዲያና ማኅበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም በሕሙማን እና በቤተክርስቲያን ስም የሚከናወኑ ልመናዎች ለተባለው ዓላማ ስለመዋላቸው ማረጋገጥ ከእያንዳንዱ እርዳታ ሰጪ ይጠበቃል ብለዋል ብፁዕ አቡነ አብርሃም።
ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን በጣስ መልኩ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን እና ሥርዓተ አምልኮ በዲጂታል ሚዲያ የሚያስተላልፉ አገልጋዮች እና ሌሎች የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸው ገልጸዋል። ብፁዕነታቸው ቤተ ክርስቲያን በቀጣይ ለዲጀታል ሚዲያና ማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን በተመለከተ የራሷን ሕግና መመሪያ እንዲዘጋጅ ይደረጋል ብለዋል።
ብፁዕነታቸው መርሐ ግብሩን ላሰናዳው በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ምስጋና አቅርበዋል።

መርሐ ግብሩ ሚያዝያ ፯ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በሚያስተላልፉት አባታዊ ቃለ ምእዳንና መልዕክት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።