ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ አዲሱን ዓመት አስመልክቶ ለመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው ያስተላለፉት አባታዊ መልእክት።
ጳጉሜን 4/2016 ዓ/ም
===============
እንኳን ከዘመነ ቅዱስ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ቅዱስ ማቴዎስ በሰላምና በጤና አሻገረን አሻገራችሁ። “ወይቤሎ ኅድጋ እግዚኦ ሐሪፈኒ’ “በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት” ሉቃ 13፥8
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ ባስተማረው በዚህ ትምህርት ውስጥ የአትክልቱ ባለቤት፡ በወይኑ አትክልት ቦታ የተተከለች በለስና የአትክልቱ ሠራተኛ ይገኛሉ። የበለሷ ባለቤት በለስ መትከሉና የሚንከባከብ ሠራተኛ የመቅጠሩ መሠረታዊ ዓላማ ከበለሷ ፍሬ ለማግኘት ነው። ነገር ግን የአትክልቱ ባለቤት በለሷ ፍሬ መስጠት በሚገባት ወቅት ጠብቆ ቢመጣም ፍሬ ማግኘት አልቻለም። የአትክልት ሠራተኛውን እነሆ ከዚች በለስ ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም አላገኘሁም ቁረጣት፣ ስለምን ደግሞ መሬቱን ታጎሳቁላለች? አለው። ጠባቂዋም ‘ጌታ ሆይ ፍሬ እንድታፈራ አስፈላጊውን እስካደርግላት ድረስ በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት በማለት ልመናን አቀረበ።
የበለሷ ባለቤት በለስ ተክሎ ፍሬ እንደፈለገ ሁሉ እኛንም ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር ሲፈጥረን ፍሬ እንድናፈራ እንጂ ፍሬ አልባ በለሶች እንድንሆን አይደለም። ፍሬ ማፍራት ካልቻልን ደግሞ እጣ ፋንታችን መቆረጥ ይሆናል፡፡ ስለዚህ የንስሓ፣ የፍቅር፡ የይቅርታ የበጎ ምግባር ፍሬ እንድናፈራ ይፈልጋል። የአትክልቱ ሠራተኞች በዚች ዓመት ተዋት ብለው እንደለመኑ ዛሬም እኛ ከዓመት ወደ ዓመት መሻገራችን በጎ ፍሬ ስለ ተገኘብን ሳይሆን ፍሬ እንድናፈራ አቤቱ የዘንድሮን ተዋት በማለት በሚማልዱልን በቅዱሳን መላእክት ምክንያት መሆኑን ማስተዋል ይገባናል። ፍሬ ሳታፈራ ለምን ምድርን ታጎሳቁላለች እንደ ተባለችው በለስ እኛም እንንከባከባት ዘንድ የተሰጠችንን ምድር በክፋት፡ በጥላቻ፡ ፍቅርን ትተን ጠብን በመዝራት እርስ በርእስ በመጠፋፋት ለሰው ልጆች የመከራና የሰቆቃ ስፍራ አድርገናታል፡፡ ክቡር የሰው ልጅ ደም በራሱ በሰው ልጅ ጭካኔ በከንቱ እየፈሰሰ ይገኛል፡፡ ፍሬ ባያገኝብንም እግዚአብሔር ቸር በመሆኑ በቅዱሳን ጸሎት ከዘመነ ቅዱስ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ቅዱስ ማቴዎስ እንድንሻገር ፈቀደልን። በመሆኑም ይህ ዘመን የተጨመረልን ለንስሐ የሚገባ ፍሬን እናፈራ ዘንድ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ከዘመን ወደ ዘመን መሻገር በሰዎች ጥበብ የማይገኝ ከእግዚአብሔር ብቻ የሚሆን ትልቅ ስጦታ ነው። እግዚአብሔር ደግሞ በጊዜ ላይ ጊዜ በእድሜ ላይ እድሜ የጨመረልን ካለፈው ዘመን ተምረን የሚቀጥለውን በማረም ፍሬአማ ሕይወትን መኖር እንድንችል ነው፡፡ በአዲሱ ዘመን ሰላምና ፍቅርን በሀገራችን ለማጽናት የበኩላችንን ማበርከት ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ በ2017 ዓመተ ምሕረት በዘመነ ቅዱስ ማቴዎስ ጥላቻን አርቀን ፍቅርን፣ ክፋትን ትተን ደግነትን፡ መገፋፋትን አስወግደን መረዳዳትን፡ ከኃጢአት ርቀን ጽድቅን የምንሠራበት፣ ጦርነት ከሀገራችን ተወግዶ በሰላም ወጥተን በሰላም የምንገባበት፡ መለያየታችን ወደ አንድነት የሚመጣበት ዘመን እንዲሆን በጸሎት ትተጉ ዘንድ አደራ ጭምር አሳስባችኋለሁ፡፡
የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ዘመነ ቅዱስ ማቴዎስን የሰላምና የበረከት ያድርግልን፡፡ አሜን
መልእክተ ሕይወት ኢየሱስ ክርስቶስ ሀገራችንንና ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅልን!!!
አባ ዮሴፍ
የሲዳማ ሀገረ ስብከት እና የሀዋሳ ታቦር ፍኖተ ጥበብ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል።