ታኅሣሥ 7 ቀን 2016 ዓ.ም
===

ታኅሣሥ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ብፁዕ አቡነ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ስራ አስኪያጅ የባሕር ዳርና ሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሓፊና የኒውዮርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት እና የደቡብ ኦሞ ጅንካ ፣ የአሪ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ብፁዕ አቡነ ሰላማ የምዕራብ ጎንደር ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም መልአከ ምሕረት ዘካርያስ ሐዲስ የየካና ለሚ ኩራ ክፍላተ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሪ ምሥራቀ ጸሐይ ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ተገኝተው የሕንፃ ግንባታው ሒደት ጎብኝተው መንፈሳዊ አገልግሎት ሰጥተዋል።

የደብሩ አስተዳዳሪ እና ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን የሰ/ት /ቤት ወጣቶች እና ምእመናን በተገኙበት ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የነበረውን ታላቅ የስብከተ ወንጌል ጉባኤ ላይ በብፁዓን አበው ሊቃነጳጳሳት ትምህርተ ወንጌል በማስተማርና በተለያየ መንፈሳዊ አገልግሎት አበርክተዋል።
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳቱ ከተጀመረ አንድ ዓመት እንደ ሆነ በተገለጸው አዲሱ የሕንፃ ቤተክርስቲያን ግንባታን ጎብኝተዋል።

በመርሐ ግብሩ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ዮሐ.1፥ 44 ተጽፎ የምናገኘው ኃይለ ቃል ” ነቢያት ስለ እሱ የተናገሩትን መሴ ስለሱ የጻፈለትን አግኝተነዋል ” በሚል ርእስ ያስተማሩ ሲሆን ወደ ቤተክርስቲያን ስንቀርብ እውነተኛውን አምላክ ነቢያት ስለእሱ ብዙ ያሉለትን እናገኘዋለን ብለዋል።

በመቀጠልም ብፁዕ አቡነ አብርሃም የምእመናኑ አስተዋጽኦ ለሕንጻ ግንባታ የላቀ መሆኑን በመጥቀስና በ1ኛ ዜና መዋእል 28፥6 ያለውን ኃይለ ቃል ” እርሱም ልጅ ይሆነኝ ዘንድ መርጬዋለሁና እኔም አባት እሆነዋለሁ ልጅህ ሰሎሞን ቤቴንና አደባባዮቼን ይሠራል ” በማለት እኛ የእግዚአብሔር ልጆች የሆንን የማይጠፋ ለዘለዓለም ሕይወት ስንቅ የሚሆነን ቤተ እግዚአብሔር በመሥራት አምላካዊ ቃሉን ልንተገብር ይገባል በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የደብሩ አስተዳዳሪ ጉባኤ ሊቀ ብርሃናት ናሁ ሰናይ ነጋ በሀገር ውስጥም በውጭ ዓለም ያሉ የሥላሴ ወዳጆች የተጀመረውን የሕንጻ ቤተክርስቲያን ግንባታ መደገፍ እንደሚገባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመጨረሻም በብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ ቃለ ምዕዳን እና ቡራኬው መርሐ ግብሩ ተጠናቋል።

©EOTC TV