ጥቅምት ፬ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
“””””””””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
******
ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስአበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል የበላይ ጠባቂ ሊቀ ጳጳስ እና ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሰ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ የፍ/ደ/መዊዕ ቅዱስ ገብርኤልና ቅድስት አርሴማ ሰበካ ጉባኤ ለሚያሳንጸው ሕንጻ ቤተክርስቲያን የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ።

በደብሩ የነበረው አለመግባባትን ተከትሎ ይታይ የነበረው የመልካም አስተዳደር ችግር ከመሰረቱ ተወግዶ የስብከተወንጌልና የልማት ሥራ በስፋት እየተከናወነ የሚኝበት ይኸው ደብር በአንድ ዓመት ተገንብቶ የሚጠናቀቅ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ለመገንባት ጥረት እየተደረገ ሲሆን ለግንባታው የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች ተሰባስበው የባለሙያዎች ኮሚቴ ተቋቁሞ ግንባታው የሚፋጠንበት ሁኔታ መመቻቸቱን የደብሩ አስተዳዳሪ ሊቀ ማዕምራን ሥነጸሐይ መለስ ገልጸዋል።

በደብሩ የነበረው ችግር በመሰረቱ ከመወገዱ በተጨማሪ በደብሩ ሰፋፊ የስብከተወንጌል መርሐ ግብር እየተካሔደ በመሆኑ ሕዝበ ክርስቲያኑ በስፋት ወደ ቤተክርስቲያን እየመጣ ይገኛል ያሉት የደብሩ አስተዳዳሪ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግም አዲስ ሞንታርቦ ተገዝቶ ጥቅም ላይ መዋሉንና ቅጽረ ቤተክርስቲያኑን ለማስከበርም ዙሪያው እንዲታጠር መደረጉን ጨምረው አስታውቋል።

አያይዘውም በዚህ ወቅት በደብሩ የተመዘገበው የስብከተ
ወንጌልና የልማት ሥራ እንዲጠናከር እንዲስፋፋ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ያደረጉልን የክፍለ ከተማችን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሰ ስለሆኑ ልዩ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

በዚሁ መርሐ ግብር ላይ ለደብሩ ሥራ መስፋፋት፣ለሰላሙና ለስብከተወንጌሉ መጠናከር አስተዋጽኦ ያበረከቱ ካህናት፣ሊቃውንት፣የሰበካ ጉባኤ አባላት በሊቀ ማዕምራን ሥነጸሐይ መለስ በግላቸው የተዘጋደላየውን ሽልማት ከብፁዕ አቡነ ሄኖክ እጅ የተቀብሉ ሲሆን ከደብሩ ሰበካ ጉባኤ ጽሕፈት ቤት ለብፁዕ አባታችን አቡነ ሄኖክ፣ለሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሰና ለሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች የተዘጋጀው ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ሄኖክ ቃለምዕዳን፣ ቃለበረከትና ቃለ ቡራኬ ሰጥተው የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል።